ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ያቀረበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ ማግኘት መጀመሩን፤ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለአሐዱ አስታውቋል።

"በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና እርቅን ለማምጣት ምን ያክል ርቀት ሄዳችኋል? ውጤታማነቱስ በተጨባጭ ምን ይመስላል?" ሲል አሐዱ የጉባኤው ተቀዳሚ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለን ጠይቋል።

ተቀዳሚ ጸሐፊው በሰጡት ምላሽ፤ "የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ የሚገኘው ግጭት እንዲቆም እና ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጡ እንዲሁም እንዲደራደሩ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል" ብለዋል።

ጥረቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበር በሁለቱ ወገኖች መለካከል ያለዉ አለመተማመን እና የመደራደር ፍላጉት ያለማሳየት ችግሮች ቢስተዋሉም፤ ጉባኤዉ የጀመረውን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

"የቀረቡት የሰላም ጥሪዎች ሁሉ የሚፈለገውን ውጤት እያስመዘገቡ ባይሆንም ግጭት በነበረባቸው አንዳንድ የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች ለጉባኤው የሰላም ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እየተገኘ ነው" ያሉት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ "ጉባኤዉ አለመረጋጋት በሚስተዋልባቸዉ አንድ አንድ አከባቢዎች አሁንም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪን ያቀርባል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሰላም እና ጸጥታ መከበር የሚበጀውን ሁሉ ከማድረግ እንደማይቆጠብና ከዚህ በኋላም የሰላም ጥሪዎች እንደሚቀጥሉ ተናግረው፤ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች ለሰላም ጥሪው በጎ ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

"ነፍጥ ላነገቡ እና ለታጠቁ አካላት በተደጋጋሚ ለምናደርጋቸው ጥሪዎች ተግባራዊ መደረግ ታዲያ መንግሥት እና ሕዝብ ሀላፊነት ሊወስዱ ይገባል" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

"በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሕዝቦች ከባድ ፈተና ሁኗል" ያሉት ተቀዳሚ ጸሐፊው፤ በሁሉም ወገን ከምንም በፊት ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጥ አሳስበዋል።

በዚህም መሠረት ሁሉም አካላት ጉዳዮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በማድረግ መነጋገሩና መደራደሩ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፤ ለሁሉም ወገን ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ