ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ መካከል ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ የተደረገውን የጋራ መግባባት በአወንታዊ መልኩ እንደሚመለከተው የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል፡፡

"የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድን ማስተናገድ ትልቅ ምዕራፍ ነው" ሲልም ነው ሕብረቱ የገለጸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ያደረጉትን የሁለትዮሽ ስብሰባ “ወሳኝ ኩነት” ሲሉ፤ የአፍሪካ ሕብረት በሶማሊያ የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ተወካይ መሀመድ ኤል አሚን ሶፍ አድንቀውታል፡፡

ውይይቱ "ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ወደ ማሳደግ፣ የፀጥታ ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውህደትን በማስተዋወቅ ላይ የታደሰውን ትኩረት አስፈላጊነት ያሳያል" ብለዋል።

"የግዛታዊ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና የጋራ ብልጽግናን ለማራመድ ወሳኝ ነው" ሲሉም ተወካዩ አክለዋል።

ሁለቱ መሪዎች በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ለአንድ ዓመት የዘለቀውን አለመግባባት እንዲቆም በማድረግ፣ በየመዲናቸው ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና እንዲኖር መወሰናቸው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ እና ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የተፈጠረው እ.ኤ.አ ጥር 2024 ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጣይ ከሶማሌላንድ ጋር የቀይ ባህር በርበራን ወደብ ለመጠቀም ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በዚህም ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሉኣላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ድጋፍ እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ብትገልጽም፤ ቱርክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ በትጋት ሽምግልና በማድርግ የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን ፊት ለፊት በማገናኘት ለችግራቸው ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ