ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባዔ ጽ/ቤት፤ ከነገ እሁድ ታሕሳስ 27/2017 ጀምሮ እስከ ጥር 2/2017 ድረስ የሚቆይ "ልዩ የሆነ ወደ አላህ የመመለስና መልካም ሥራዎች እየሰሩ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ዱዓ የማድረግ ቀን ተግባራዊ እንዲደረግ" ጥሪ አቅርቧል።

የዑለማ ጉባዔ ጽ/ቤቱ ለጠቅላላው ሕዝበ ሙስሊም ባስተላለፈው መልዕክት፤ "ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰው ሰራሽን በተፈጥሮ ችግሮች ምክንቶች እየታመሰች ትገኛለች።" ብሏል።

"ለዚህም ዋና ምክንያቱ የሰው ልጆች የርስ በስርስ ፍቅር መጥፋት፤ ጥላቻ መስፋፋት የእርስ በርስ መገዳደል መበራከትና የሰው ልጅ ነብስ ከምን ጊዜውም በላይ ርካሽ የሆነበትና በቀላሉ ሕይወት የተቀጠፈ የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡" ሲልም ገልጿል።

"ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጥፋቶቻችንና ከስህተቶቻችን ለመመለስ ባለመቻላችን ምክንያት ተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመከሰት ላይ ይገኛሉ፡፡" ያለው ጽ/ቤቱ፤ ለአብነት ያህልም ባለፈው ክረምት በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፤ እንዲሁም በአማራ ክልሎች በተከስተው የመሬት መንሸራተት በርካታ ሰዎች መሞታቸውና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አንስቷል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ በሀገሪቱ እየተከሰተ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ "ይህ ሁሉ ክስተት እኛ የሰው ልጆች በምንሰራቸው ወንጀሎች ሳቢያ የሚመጡ ክስተቶች በመሆናችው ነው" ብሏል።

በዚህም ምክንያት ከፊታችን እሁድ ታሕሳስ 27 ቀን2017 ጀምሮ እስከ ጥር 2 ቀን 2017 ድረስ የሚቆይ ልዩ የሆነ ወደ አላህ የመመለስና መልካም ሥራዎች እየሰሩ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ዱዓ የማድረግ ቀን ተግባራዊ እንዲደረግ የኡለማ ጉባዔ ጽ/ቤት ለመላው ሕዝበ-ሙስሊም የሚከተሉትን መልእክቶች አስተላልፏል፡፡

በዚህ መሰረት ፦

1. ሕዝበ-ሙስሊሙ በአጠቃላይ ተውበት በማድገረግ ወደ አላህ እንዲመለስ

2. ሁላችንም እርስ በርስ ይቅርታ እንድንባባል፤

3. ለተቸገሩትና ረዳት ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሶደቃ ( ምጽዋት) መስጠት

4. በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ አጠቃላይ መስጂዶች በየአምስት አውቃት ሶላቶች ላይ ቁነት እንዲደረግ፤

5. የቀጣዩ ጁሙአ ቀን በሁሉም መስጂዶች የሚደረጉ ኹጥባዎች በዚህ ዙሪያ እንዲሆኑና አጠቃላይ ዱዓ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡