ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የርዕደ መሬት ክስተት የተፈጥሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደወለን ተከትሎ፤ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በክልሎቹ እየተከሰተ ባለው የርዕደ-መሬት ክስተት ሁኔታና ምላሽን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ በእስካሁኑ ሁኔታና ምላሽ እየታየ ያለው ሥራ አመርቂ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሠረት በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች ማለትም አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ (ዱለሳ) ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው ተመላክቷል።

በሁለቱም ወረዳዎች ማለትም በአዋሽ ፈንታሌ 6 ተጋላጭ ቀበሌዎች 15 ሺሕ ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ እስከ አሁን 7 ሺሕ ወገኖች ከስጋቱ ቀጠና ወደ ሌላ ስፈራ መጓጓዛቸው ተገልጿል፡፡

በዱለቻ ወረዳ ደግሞ 20 ሺሕ የሚሆኑ የ2 ቀበሌዎች ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ቀበሌዎች እስከ አሁን 6 ሺሕ 223 ሕዝብ አካባቢውን መልቀቃቸው ተነግሯል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የ5 ቀበሌዎች ወገኖች ለአደጋው ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።

በ5ቱም ቀበሌዎች 16 ሺሕ 182 ሕዝብ ተጋላጭ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ 7 ሺሕ 350 ሕዝብ ከተጋላጨ ስፍራ መውጣታቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም 8 ሺሕ 832 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ፤ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ክስተቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ የሳይንቲፊክ ኮሚቴ፣ ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ ሲሆን፤ መገለጽ ያለበትን ቅድመ-ጥንቃቄዎች አስመልከቶ አስፈላጊው መረጃ ለሕዝብ በተከታታይ እንደሚቀርብ አስታውቋል፡፡

ይህንንም ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማህበራዊ ሚዲያዎችና ድህረ ገጽ መከታተል ይቻላል ተብሏል፡፡

የርዕደ መሬት ንዝረቱ ባለበት አካባቢ ያለ ማህበረሰብ ከንዝረቱ በፊት፣ በንዝረቱ ወቅትና ከንዝረቱ በኋላ ያለውን መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄ እንዲወስዱ አስፈላጊው መረጃ እየተሰጠ እንደሚገኝም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ እስከ አሁን ለ70 ሺሕ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን 1 ሺሕ 550 ኩንታል ምግብ-ነክ እና ለ7 ሺሕ አባወራ የሚሆን ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው መላኩ ተገልጿል፡፡

ይህም በገንዘብ ሲተመን ለምግብ 216 ሚሊዮን 562 ሺሕ 500 ብር እና ምግብ-ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች 65 ሺሕ 625 ሺሕ ብር በድምሩ 281 ሚሊዮን 562 ሺሕ 500 ብር የሚገመት መሆኑ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የርዕደ መሬቱን ባህሪያትና የሚጠይቀውን የጥንቃቄ መልዕክቶች በተከታታይ እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን፤ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ አደጋውን ለመሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በንቃት እንዲንቀሳቀሱ አሳስቧል፡፡