የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት) የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅን፣ የመመሪያውን ደንጋጌዎችና የቦርዱን ውሣኔዎች በማክበር የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅና አመራሮቹን ሳይመርጥ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ከምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች መታገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ፓርቲው በዐዋጅና መመሪያው ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ባለማክበር ጉልህ ጥሠት በመፈጸሙ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016ን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀጽ 18(1) መሠረት፤ ፓርቲው ይህ ውሣኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሣተፍ እንዲታገድ ቦርዱ ወሥኗል።

ፓርቲው ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሠት በማረም፤ ዐዋጁን፣ ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ፣ የቦርዱን ውሣኔዎችና ትዕዛዞች በማክበር ፓርቲው ሊያደርግ የሚገባውን ጠቅላለ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችለውን የጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅና ቦርዱ ይህንኑ ሲያረጋግጥ በመመሪያው አንቀጽ 18(2) መሠረት ቦርዱ ዕግዱን የሚያነሣ መሆኑን መወሰኑን ገልጿል።

ፓርቲው በተሰጠው የሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3(11)(ሐ) እና በመመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀጽ 19 (1) (ሐ) መሠረት ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ ቦርዱ መወሰኑንም በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ