የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከሰሞኑ በህወሓት እና በጊዚያዊ አስተዳደሩ አካላት መካከል ስምምነት እንደተፈጸመ ተደርጎ የተገለጸው ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
"በጊዜያዊ አስተዳድሩና በህወሓት መካከል ተደረገ የተባለው የእርቅ ጉዳይ በመሠረቱ ግልፅነት ይጎድለዋል" ያሉት የባይቶና አባይ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ክብሮም ተክላይ፤ "የአስተሳሰብ ልዩነት የሌላቸው፣ የአቋምም ልዩነት የሌላቸው ሰዎች በመሆናቸው ልዩነታቸው ስልጣን ብቻ ነው" ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በሐይማኖት አባቶች የሚደረግ የእርቅ ሙከራ ጊዚያዊ ለውጦችን ሊያመጣ የሚችል ቢሆንም፤ ዘላቂ መፍትሄን ያመጣል የሚል ዕምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡
ተደረገ የተባለውም ስምምነት የሥነ-ምግባር ደንብ መሆኑን የገለጹት አቶ ክብሮም፤ ስምምነቱ ‘ወደ ጦርነት ከሚመሩ ምግባሮች እንዲሁም አላስፈላጊ ፕሮፓጋንዳዎች መቆጠብ' የሚል መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
"የህወሓት ልዩነት በክልሉ ላይ የሚታዩ ልነቶችን እየፈጠረ ነው" የሚሉት አቶ ክብሮም፤ "የፓርቲው እርቅ የትግራይ እርቅ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
"ይሁን እንጂ አሁንም ሁለቱ አካላት ልባዊ እርቅ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው አይመስልም" ያሉት የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ አባል፤ ይህ ሂደት መስተካከል እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡
"ጥር 12 2017 በወጣ ደብዳቤ ስምምነት ስለመፈረማቸው ይገልጻል" የሚሉት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ብርሃነ አፅብሃ በበኩላቸው፤ "መግለጫው ደግሞ ከወር በኃላ የካቲት ላይ የወጣ በመሆኑ ከልብ የተደረገ አለመሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡
በህወሓት ጉዳይ እርቅ ተብሎ እየቀረበ ያለው ጉዳይ በተለይም ሕግና መርህን ጭምር የተከተለ አለመሆኑን የሚያኑሱት አቶ አብርሃ፤ "ስምምነቱ እውነተኛ አይደለም" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"በተጨማሪም ‘እርቅ ተደረገ' ተብሎ የሚዘገበውም ተገቢ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ የተፈጸመው የሥነ-ምግባር ደንብ ላይ የተደረገ ሰምምነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተለይም ሃይልን ላለመጠቀምና ሕዝብን ወደ ግጭት ከሚወሰዱ ንግግሮች እራስን መቆጠብ እንደሚገባ አቶ ብርሃነ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በመቀሌ የህወሓት አመራሮች ሁሉን አቀፍ ችግሮቻቸውን በሰላምና በውይይት ለመፍታት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን በተመለከተ የሐይማኖት አባቶች መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በህወሓት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የተደረገ ስምምነትም ሆነ እርቅ የለም ሲሉ ፓርቲዎች ገለጹ
