ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከገዢው ፓርቲ ጋር ውይይት የምናድርግበት ነጻ የሃሳብ መድረክ ሊዘጋጅ ይገባል ሲሉ፤ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጠይቀዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ማካሄዱ የሚታወቅ ሲሆን፤ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ "የኢትዮጵያ የፓርቲና የፓለቲካ ስርዓት ወቀሳ የበዛው ነበር" ብለዋል።

አክለውም "ከሳሽ አማራሪ እንጂ አዲስ ሀሳብ ይዞ የመጣ ፓርቲ የለም" በማለት፤ "ሀሳብ የለሽ ፓለቲከኞች ሀሳብ የለሽ ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ ድል የረጅም ጊዜ መከራን ይዘው ይመጣሉ" ሲሉ ወቀሳ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሐዱም "ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጉባኤው ለራሳቸው ምን የቤት ሥራ ወሰዱ?" ሲል ጠይቋል።

የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አመራርና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሙባረክ ረሺድ፤ "በአጠቃላይ 'ፓርቲዎች ሀሳብ የለሽ ናቸው' ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይደለም" ብለዋል።

አክለውም "ብሽሽቅ የሌለበት ነፃ ሀሳብ የሚንሸራሸርበት መድረክ ከገዢው ፓርቲ ጋር ሊዘጋጅልን ይገባል" ያሉ ሲሆን፤ " 'ክሶች በዝተዋል' ከሚሉ ንግግሮች ባሻገር ይህን መሰል መድረክ በማዘጋጀት ሀሳባችንን መግለጽ እንችላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ "ፓርቲዎች ሀሳብ የላቸውም ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም ስለ ፓሊሲዎችና ሌሎችም ጉዳዮች ካሉ፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

"ኢትዮጵያ የሁሉም ናት" ያሉት ፓለቲከኛው፤ "ለሀገር የሚበጁ ጉዳዮችን በመናገራችን ከሳሾች መባል የለብንም" ሲሉ ገልጸዋል።

ቀድሞውኑም የሀሳብ ተሰሚነት አለመኖርና እና የፓለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ራሱ ሌላው ተግዳሮት መሆኑንም አንስተዋል።

"ፓርቲው በራሱ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ አይደለም" ያሉት ፓርቲዎቹ፤ "በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደረጉ ንግግሮች የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ ቅቡልነት የሌለው ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ