ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደው በሚገኘው 15ኛ መደበኛ ጉባኤው፤ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሹመትን መርምሮ በአንድ ድምፅ ተዓቅቦ በሙሉ ደምፅ አጽድቋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካሉት ሰባት ምክትል ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ የሆኑት ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በምክር ቤቱ ተመርጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት መሐመድ እድሪስ አቶ ብናልፍ አንዷለምን በመተካት፤ የሰላም ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።
በዚህ መሠረት ዶክተር ሳምሶን አቶ መሐመድን ተክተው የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በመሆን የሚሰሩ ይሆናል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዋና ዳይሬክተሩን ሹመት እንዲያጸድቅ፤ ጥያቄውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 1 በጽህፈት ቤታቸው አማካኝነት ለፓርላማ በላኩት ደብዳቤ፤ የሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ሹመት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አማካኝነት እንዲከናወን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡