ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በስድስት ወራት ውስጥ ከ32 ሚሊየን 6 መቶ ሺሕ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ የሚያወጡ ምግብና ጤና ነክ ምርቶች እንዲሁም የተበላሹ ቁሳቁሶችን እንዲወገዱ መደረጉን የአዲስ አበባ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት በ 6 ወራት ውስጥ ከ32 ሚሊየን 627 ሺሕ 459 ብር ግምታዊ ዋጋ የሚያወጡትን እነዚህን ምርቶች ማስወገድ መቻሉንም ነው የገለጸው፡፡

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ11 ቅርንጫፍ እና በማዕከል ደረጃ በ26 ሺሕ 552 የምግብ እና ጤና ነክ አምራች ኢንደስትሪዎች ላይ የቁጥጥር ሥራ ማከናወኑን ገልጿል፡፡

የሕገወጥ እርድ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ እርድ መገኘት፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች መገኘት እና የተወሰኑ ነጋዴዎች ምርቶች ከሌላ ምርት ጋር ቀላቀሎ መገኘት በክትትል ወቅት የተያዙ ዋና ዋና ክፍተቶች መኖቸው ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተከናወነ የቁጥር ሥራዎች በ466 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጿል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው ከ4 መቶ በላይ ተቋማት ውስጥ በ372 የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ92 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ የተደረገ ሲሆን፤ በ2 ተቋማት ላይ ከተፈቀደላቸውና ከተሰጣቸው ብቃት ማረጋገጫ ውጭ ሆነው ሲሰሩ በመገኘታቸው ምክንያት ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡