ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት ስድሥት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲፈፅሙ በተገኙ ከ108 ሺሕ በላይ የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

እነዚህ የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ከውጪ ምንዛሬ ማሻሻያው ሂደት ጋር ተያይዞ ያለአግባብ ለመበልፀግ ሆን ተብሎ በሸማቹ ላይ ተገቢ ያልሆነ ውዥንብር በመፍጠር፣ ምርት በመሰወርና ዋጋ እንዲንር በማድረግ ላይ የተሳተፉ ሕገወጦች መሆናቸውን በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊቁ በነበሩ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ይህንን ድርጊት ለመግታት ከፌዴራል እስከ ታችኛው እርከን ያለውን የንግድ መዋቅር በማነቃነቅ በተደረገ ከፍተኛ ርብርብም ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ባለው ሂደት በጥቅሉ 108 ሺሕ 311 የንግድ ድርጅቶች እና ነጋዴዎች ላይ እርምጃዎች በመወሰድ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ሲሉም ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 55 ሺሕ 94 የሚሆኑት ድርጅታቸው የታሸገ ሲሆን፣ 51 ሺሕ 269 ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፣ 932 የንግድ ፈቃድ ስረዛና እገዳ እንዲሁም አንድ ሺሕ 16 የሚሆኑት ላይ ደግሞ እስራትና ገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

ድርጅታቸው ከታሸገባቸው ውስጥ 54 ሺሕ 487 የሚሆኑት የስምምነት ውል ገብተው እንዲከፈቱ መደረጉንና ከታሰሩት ነጋዴዎች ውስጥ ደግሞ አንድ ሺሕ 14 የሚሆኑት የስምምነት ውል ከመግባታቸው ባሻገር ገንዘብ ተቀጥተው እንዲለቀቁ መደረጉን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በዚህ ስድሥት ወራት ውስጥ ነዳጅን ጨምሮ ከተወረሱ ምርቶች ሽያጭና በሕገ-ወጦች ላይ በተወሰደ የገንዘብ ቅጣት ከ56 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ለአሐዱ በሰጡት መረጃ አስረድተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ፈላጊ ነጋዴዎች በኢንዱስትሪና የግብርና የፍጆታ ምርቶች ላይ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ በየደረጃው በተዋቀረ የሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረሀይል እርምጃ በመውሰድ ወደ ሕጋዊ አሰራር እንዲገቡ በጥብቅ ክትትል እየሰራበት እንደሚገኝም አፅንኦት ሰጥተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ