ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሩሲያ ከኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያና ቱኒዚያ ጋር በሀገር ውስጥ ገንዘብ ለመገበያየት የሚያስችል ስምምነት ማድረጓን ክሬምሊን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት ሩሲያ ሦስቱን ሀገራት በሰሜን እስያ ሀገር ለንግድ መገበያያ ብቁ ከሆኑ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ማካተቷ ተነግሯል።
ይህን ስምምነት ተከትሎም አሁን በሞስኮ ምንዛሬ እንዲገበያዩ የተፈቀደላቸው ሀገራት ወደ 40 መድረሳቸውን ክሪምሊን ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያሉት አገራት ዝርዝር 30 ያህል ነበር።
እንደ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በመስከረም ወር 2023 በሩሲያ መንግሥት የጸደቀው የመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ ነበሩ።
አሁን ላይ የአርጀንቲና፣ የካምቦዲያ፣ የላኦስ፣ የሜክሲኮ፣ የናይጄሪያ፣ የቱኒዚያ እና የኢትዮጵያ የንግድ ተወካዮች በመገበያያ ገንዘብ ንግድ እንዲሰማሩ አዲስ ፈቃድ ማግኘታቸውን መግለጫው አስታውቋል፡፡
የሩስያ መንግሥት መመሪያው የሩስያ ኢኮኖሚን በመገበያያ ገንዘብ የሚከፍለውን ፍላጎት ለማሟላት እና ወዳጃዊ እና ገለልተኛ መንግሥታትን ብሄራዊ ገንዘቦች በቀጥታ ለመለወጥ የስርዓቱን ውጤታማነት እንደሚያሳድግ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ሀገራቱ ከሩሲያ ጋር በሚፈጽሙት ግብይት የሚያጋጥማቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እና የተሻለ የንግድ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ማስታወቁን የስፑትኒክ ዘገባ አመላክቷል፡፡
ሩሲያ ዋና ተሳታፊ የሆነችበት የብሪክስ አባል ሀገራት ቡድን፤ የፋይናንስ ተቋም እና ነጻ የግብይት ስርዓት ለመፍጠር ባስቀመጠው ዕቅድ መሰረት የአሜሪካ ዶላርን የሚተካ አለማቀፋዊ የመገበያያ ገንዘብ በመፍጠር የራሱን የመገበያያ ገንዘብ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡
ይህም የአሜሪካ አዲሱን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ትኩረት የሳበ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም ትራምፕ በብሪክስ አባል አገራት ላይ 100 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ለመጣል ዝተዋል፡፡
በምላሹም ክሬምሊን አሜሪካ ሀገራትን ለማስገደድ የምትሞክር ማንኛዉም ሙከራ ያልተጠበቀ ውጤት እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ