ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዘንድሮው ዓመት በላሊበላ ከተማ በተከበረው የገና በዓል ላይ፤ ከ888 ሺሕ በላይ ሰዎች መገኘታቸውንና በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ በሰላም መጠናቀቁን የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።
የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል አስመልክቶ በከተማዋ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ፤ ከ495 በላይ የውጪ ሀገራት ጎብኚዎች መሳተፋቸውንም የመምሪያው ኃላፊ ገነት ሙሉጌታ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ከውጪ ሀገራት የመጡ ታዳሚዎችን በመቀበል እግር አጥቦ ማስተናገዱን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላም በሬ አርዶ አብልቶና አጠጥቶ መሸኘቱን አክለው ገልጸዋል።
"የዚህኛው ዓመት የገና በዓል አከባበር እንከንየለሽ ነበር" የሚሉት ኃላፊዋ፤ የተረጋጋ ከነበረው የሰላምና ፀጥታ ባሻገር ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ አለመከሰቱን አንስተዋል።
ከታሕሳስ 26 እስከ 28 ባሉት ቀናት ከ17 በላይ በረራዎች ወደ ከተማዋ መካሄዳቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
"በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ተቀዛቅዞ የነበረው የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ አሁንም በክልሉ ባለው ግጭት ሳቢያ በእጅጉ እንደተጎዳ ነው" ያሉት ኃላፊዋ፤ ሰላም ለቱሪዝም እድገት ወሳኝ እንደመሆኑ ዘርፉ ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሙት አስረድተዋል።
በመሆኑም በዘንድሮው ዓመት የተከበረው የገና በዓል ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ካሉ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር፤ የተሻለና ቱሪዝሙን ማነቃቃት የሚችል ጥሩ የሚባል ፍሰት የታየበት እንደነበር ገልጸዋል።