ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ምዕራብ ቻይና ቲቤት ግዛት በትናትናው ዕለት በተከሰተ ከባድ የርዕደ መሬት አደጋ ከ126 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

በትናንትናው ዕለት በቻይናዋ በሂማላያ ተራሮች ሥር በምትገኘው ቲቤት ግዛት በተከሰተው ከባድ የርዕደ መሬት አደጋ ምክንያት በርካታ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በፍርስራሾች ውስጥ የነበሩት ከ400 በላይ ሰዎች በተደረገ ርብርብ ሊተርፉ መቻላቸውን የሀገሪቱ የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

Post image

ነገር ግን አሁንም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም የተባለ ሲሆን፤ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ፍለጋ ለመቀጠል ከ1 ሺሕ 800 በላይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንዲሁም 1 ሺሕ 600 ወታደሮች አደጋው ወደተከሰተበት ቲቤት ግዛት መግባታቸው ተነግሯል፡፡

በግዛቷ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት ርዕደ መሬቶች እጅግ ከባዱ ነው የተባለለት ይህ ርዕደ መሬት፤ በሬክተር 6.8 የተለካ ሲሆን፤ በዓለም ትልቅ ከሆነው የኢቨረስት ተራራ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቲቤት ውስጥ ትንግሪ በተባለች ቦታ ነው መነሳቱም ነው የተገለጸው።

Post image

ከአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ 10 ኪሎ ሜትር (ስድስት ማይል) ጥልቀት ያለው የመሬት መንቀጥቀጡ ከቲቤት አልፎም እስከ ጎረቤት ቡትሀን፣ ህንድ እና ናፓል ድረስ ዘልቆ የተሰማ ሲሆን፤ በሃገራቱም ህንጻዎችን ማንቀጥቀጡ ተነግሯል፡፡

በቤጂንግ ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ባለችው ቲቤት በአሁኑ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት የተገደበ ሲሆን፤ ዘጋቢዎች ያለመንግሥት ፍቃድ ወደ አካባቢው መሄድ እንደማይችሉ ቢቢሲ ዘግቧል።

ስለ የመሬት መንቀጥቀጡ እና ስላስከተለው ጉዳት መረጃዎችን እያወጡ የሚገኙት የቻይና መንግሥት ሚዲያዎች ብቻ ስለመሆናቸውም ዘገባው አመላክቷል።

Post image

በመንግሥት ባለቤትነት የተያዘው ፒፕልስ ዴይሊ ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ለአደጋ ተጋላጭ ሰዎች ከግዛቱ ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ሲሆን፤ በግዛቱ የኤሌክትሪክ እና የሞባይል ስልክ አገልግሎት ዛሬ ጠዋት ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለሱን ገልጿል።

Post image

የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በአደጋው ከ3 ሺሕ 600 በላይ ሕንፃዎች ፈርሰው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መጠለያ አልባ ስለመሆናቸው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።