ሕዳር 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ "ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ሱቆችን አሽገን አናውቅም" ያለ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ፤ "ከደረሰኝ ጋር ቁጥጥር እያደረገ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ነው" ሲል ገልጿል፡፡

አሐዱ "ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመርካቶ እና በሌሎች የገበያ ማዕከሎች ከደረሰኝ ጋር በተያየዘ እየታሸጉ ያሉ የንግድ ማዕከል ሱቆችን እስከመጨረሻው፤ መፍትሄ ለመስጠት ምን እየተሰራ ነው?" ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮን እና የንግድ ቢሮን አነጋግሯል፡፡

የገቢዎች ቢሮ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰዉነት አየለ በሰጡት ምላሽ፤ "ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ሱቆችን አሽገን አናውቅም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡


አክለውም "ከዚህ ጋር በተያየዘ እኛ ደረሰኝ ከመቁረጥ ውጭ ሱቆችን አሽገን አናቅም" ያሉ ሲሆን፤ "እንደ ተቋም ግን ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ የገበያ ጥናት መረጃ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ሙስማ ጀማል በሰጡት ምላሽ፤ እንደ ተቋም ግብረ ኃይል ተቋቁመዉ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

አክለውም፤ "ንግድ ቢሮ እየሰራ ያለው ከንግድ ፍቃድ ጋር በተያየዘ እና በምርት አቀርቦቶች ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ነው እንጂ፤ ከደረሰኝ ጋር በተያየዘ ጉዳይ የሚመለከተው እና ስልጣን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም ተቋማት ቀጥተኛ ኃላፊነት ከመውሰድ ቢቆጠቡም፤ ከቅርብ ቀናት ወዲህ እንደ መርካቶ ያሉ ትላልቅ የንግድ ማዕከሎችና ሱቆች "ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ እየታሸጉ ነው" የሚል ቅሬታ ሲቀርብ ይሰማል፡፡

በተጨማሪም "ይህንን ችግር በተሟላና ሕጋዊ በሆነ መልኩ እልባት እየተሰጠው አይደለም" በሚል፤ ከተለያዩ በንግድ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛል፡፡