አሐዱ ያነጋገራቸው የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካል ተወያይቶበት ከከፍተኛ የገንዘብ መቀጮ እስከ ፈቃድን መሰረዝ የሚችል ሕግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀድቀዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ሕግ መካከል፤ ዲጂታል ግብይቱን ሲያጭበረብር የተገኘ እስከ 300 ሺሕ ብር፣ የነዳጅ በርሜልን በሕገ ወጥ መንገድ በተለይም ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ሲቸረችር የተገኘ እስከ 350 ሺሕ፣ ማደያ ላይ ወይም ቦቴ ላይ ካሊብሬሽን ሲያጭበረብር የተገኘ እስከ 500 ሺሕ የሚሉት የሚገኙበት ሲሆን፤ በአጠቃላይ እስከ 700 ሺሕ ብር የሚያስቀጣ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ቅጣቱ የገንዘብ ብቻም ሳይሆን እስከ 7 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት የተካተተበት መሆኑንም አክለዋል።
ሕገወጥ የነዳጅ ግብይቱን በተመለከተ ነዳጅ ይዞ ያለአቅጣጫ ሲጓዝ ሲገኝ፣ ከማደያ በበርሜል ጭኖ ሲወጣ እንዲሁም ከዲጂታል ውጪ የገንዘብ ግብይት ሲፈፅም ቢገኝ እርምጃ እንደሚወሰድበት አስረድተዋል፡፡
እስካሁን የነበረው አካሄድ አስተዳደራዊ ብቻ በመሆኑ ባለስልጣኑ ሙሉ በሙሉ እርምጃ ለመውሰድ የተወሰኑ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶች እንደነበሩበትም ጨምረው አንስተዋል።
አሁን ላይ የነዳጅ እጥረቱ እንዲባባስ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ሕገወጥ ንግዱ በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይም ከክልል ንግድ ቢሮዎች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንና በቅርቡም ለ 229 ማደያዎች የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ዋና ዳይሬክተሯ ለአሐዱ ተናግረዋል።
እስከ 700 ሺሕ ብር የሚደርስ መቀጮና 7 ዓመት እስራት የተካተተበት ሕግ ሲፀድቅ፤ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመግታት ያስችላል ተባለ
ሕዳር 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ይገታል የተባለለት ከ 300 ሺሕ እስከ 700 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ ያለው ሕግ ወጥቶ፤ ባለፈው ሳምንት ጀምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።