የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የፋይዳ መታወቂያን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኝ የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ለአሐዱ አስታውቋል።

በተቋሙ የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር ሳሚናስ በላይነህ፤ የመንግሥት መስሪያ ቤቶቹ የፋይዳ መታወቂያን ለአገልግሎታቸው እንዲጠቀሙ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ "ይህም ጥሩ የሚባል ውጤትን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በትምህርት ቤት፣ በጤና ዘርፍ፣ በንግዱ ዘርፍና ባንኮችን ጨምሮ በበርካታ ተቋማት ላይ መመሪያው ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ በማንሳትም፤ በተለይም በቀጣይ አምስት ወራት ውስጥ በርካታ የክልል ተቋማት ላይ ከፋይዳ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

አክለውም ፋይዳ ቁጥሩ በካርድ መልክና በዲጂታል ስልክ ሁኖ በተለያየ መንገድ ሊያዝ የሚችል ቢሆንም፤ ነገር ግን በዚህ ሂደት 'ካርዱን ብቻ ካልያዛችሁ' የሚሉ እና 'የፋይዳን መታወቂያ አናቀውም' በሚል በመታወቂያው አገልግሎት እንዳያገኙ በመደረጋቸው ተገልጋዮች ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር አንስተዋል።

ነገር ግን ይህ አሰራር የተቋሙ አሰራር ባለመሆኑና ግለሰቦችም ይህን ባለማወቅ የሚፈጽሙት በመሆኑ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠትና በመንግሥት አካሄድ መሰረት አቅጣጫ በማስቀመጥ እንዲስተካከል መደረጉን ተናግረዋል።

ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት መታወቂያው በተቋማት በኩል የበለጠ ተቀባይነት እንዳለው በመግለጽ፤ እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን መመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም በአዲስ አበባ የተጀመረው የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በፋይዳ መታወቂያ እንዲሆን የማስቻል ሥራ በክልሎችም ተፈፃሚ ማድረጉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የባንኮች አሰራርን እንደ ምሳሌ በማንሳት፤ በቅርቡ በተለይም በክልል ዋና ዋና ከተሞች ላይ ፋይዳ መታወቂያን በመያዝ የባንክ ቡክ እንዲከፍቱ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ሌሎች የግል መስሪያ ቤቶች ላይም ፋይዳ መታወቂያን በማስተሳሰር ተግባራዊ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዳይሬክተሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ነዋሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንደሚያስችል የተገለጸ ሲሆን፤ መታወቂያው በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ባለ 12 አሃዝ ልዩ የፋይዳ መለያ ቁጥርን የያዘ ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ