የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ሐምሌ 19 ትምህርት ቤት አለፍ ብሎ ለሕንጻ ግንባታ የመሰረት ቁፋሮ ሥራ ላይ የነበረ የቀን ሠራተኛ አፈር ተንዶበት ሕይወቱ አደጋ ውስጥ የነበረ ቢሆን፤ የእሳት እና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው ላይ በፍጥነት ደርሰዉ ሕይወቱን ማትረፍ መቻላቸው ተገልጿል።

አደጋው ዛሬ እሁድ የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም የደረሰ ሲሆን፤ መጠነኛ ጉዳት የደረሰበትን ተጎጂ በኮሚሽኑ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት አምቡላንስ ውስጥ የሕክምና እርዳታ ተደርጎለታል ተብሏል።

Post image

በአዲስ አበባ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የአደጋ ደህንነት መስፈርት ጠብቆ ባለመስራት መሰል አደጋዎች እያጋጠሙ መሆኑን የእሳት እና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በመሆኑም አደጋውን አስቀድሞ ለመከላከል በተለይም አሰሪዎች ሥራዉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን የደህንነት መስፈርት ማሟላት እንደሚገባቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ