ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚፈጠሩ ፍል ውሃዎች ለኃይል ልማት ሊውሉ ይገባል ሲሉ የስነ ምድር ጥናት ባለሙያዎች ለአሐዱ አስታውቀዋል።
"ሀገሪቱ ከ10 ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት ጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም፤ እስካሁን ማልማት የቻለችው አነስተኛ ሜጋ ዋት ነው" ሲሉ የተናገሩት የዘርፉ ባለሙያ ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን ናቸው።
አክለውም ለጆኦተርማል ኃይል ልማት አስፈላጊ የሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የላቦራቶሪና የሰው ኃይል ግብዓቶችን በማሟላት፤ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ላይ በመሬት ውስጣዊ ሙቀትና ግፊት አማካኝነት የሚስተዋሉ ፍል ውሃዎችን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማዋል እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በዚህም ይህንን እምቅ አቅም መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መንግሥት አጽንኦት ሰጥቶ ሊያስብበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የጂኦተርማል ኃይልን ለማልማት የሚያስችላትን የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነች ቢሆንም፤ በቂ ውጤት መመልከት አለመቻሉንም ነው ባለሙያው ያነሱት።
አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ልዑልዓለም ሻኖ በበኩላቸው፤ "በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሕዝብን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ዘርፉ ወሳኝ ሚና አለው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጂኦተርማል ኃይል ከፍተኛ አቅም ካላቸው አገራት አንዷ ብትሆንም፤ ማግኘት ካለባት ጥቅም አንፃር ስንመለከት ዝቀተኛ መሆኑንም ያብራራሉ።
"ዘርፉን ሙሉ በመሉ መጠቀም ከተቻለ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት አንዷ እንድትሆን ያስችላታል" ነው ያሉት።
ባለሙያዎቹ አያይዘውም ኢትዮጵያ እና ኬንያ 90 ከመቶ የሚጠጋውን የአፍሪካን ጂኦተርማል ኢነርጂ የማመንጨት አቅም ጠቅልለው የያዙ ሀገራት በመሆናቸው፤ አጠቃቀማቸውን ካጎለበቱ የአፍሪካ የጂኦተርማል ኢነርጂ ዘርፍ ዕድገትን መምራት እንደሚችሉ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለቱሪዝም ልማትና ለሌሎች ግልጋሎቶች የሚውሉ በርካታ የፍል ውሃ ሀብቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ከሰሞኑም በአፋር ክልል በተለይም በዱለሳ ወረዳ ሳጋንቶ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በበርካታ ሥፍራዎች ላይ ፍል ውሃዎች እየተፈጠሩ እንደሚገኙ መገለጹ ይታወሳል።