ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ700 በላይ የሚሆኑ በትግራይ ክልል ሰሜን ዕዝ ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞች፤ ከሰሜኑ ጦርነት ወዲህ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ትግራይ ቅርጫፍ ለአሐዱ ገልጿል።
በሰሜን ዕዝ ሥር ይሰሩ የነበሩ ከ700 በላይ የሲቪል ሠራተኞች የሚመለከተው አካል ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ አሁንም ድረስ ተቸግረው ይገኛሉ ተብሏል።
"በራሱ የለቀቀ ሠራተኛ የለም" የሚሉት የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ፀሐዬ እምባዬ፤ "ወደ አዲስ አበባ ሪፖርት አድርጉ መባላቸው አግባብነት የለውም፡፡ የሚሰሩት መቀሌ በመሆኑ እዚሁ ሪፖርት ማቅረብ ነበረባቸው" ሲሉም ተናግረዋል።
የአራት ወራት ደመወዝም እንዳልተከፈላቸዉ የሚገልጹት ኃላው፤ "መከላከያ ሚኒስቴር በቦታዉ ተገኝቶ ያሉና የሌሉ ሠራተኞችን አጣርቶ እርምጃ መውሰድ ሲገባዉ አዲስ አበባ መታቹ ሪፖርት አላደረጋችሁም በሚል ግራ ማጋባት ተገቢ አይደለም" ብለዋል።
በሰሜን ዕዝ ሥር ይሰሩ የነበሩና ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ በሚመለከት የእንባ ጠባቂ ትግራይ ቅርጫፍ ወደ ዋናው ቢሮ እና መከላከያ ሚኒስቴር ደብዳቤ መላኩን የገለጹት አቶ ፀሐዬ፤ "ሚኒስቴሩ መጥተዉ ‘ሪፖርት ያድርጉ' የሚል ምላሽ ሰጥተውናል" ብለዋል።
"ከ700 በላይ ሠራተኞች ወደ አዲስ አበባ ከሚላክ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰባት ባለሙያ ልኮ ያሉበትን ሁኔታ ማየት ይቀላል" ሲሉም ተናግረዋል።
"ሠራተኞቹን ከመስሪያ ቤታቸው ጋር ያለያያቸዉ ጦርነት ነው" የሚሉት ኃላፊው፤ "ረጅም ዓመታት የሰሩ ባለሙያዎች ናቸው" ሲሉም ይገልጻሉ።
በመሆኑም አሁንም አራት ወራት ደመወዛቸው እንዲከፈላቸውና ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡