ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያደጉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ መንግሥት መስራት የነበረበትን የቅድሚያ ቅድሚያ ሥራዎች እየሰራ አለመሆኑን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በቅርቡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከ10 በላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ማሳደጉ ቢገለጽም፤ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት መንግሥት ከገለጸው አመክንዮ ጋር የሚፃረር መሆኑን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ዶክተር ቆስጠንጢንዮስ በርኸ ተስፋ ገልጸዋል።

በተያያዘም በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም የያዘው ውጥንም ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ከማሳደግ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ቆስጠንጢንዮስ ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ባንክ መከፈት የውጭ ኢንቨሰተሮች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና በአገር ውስጥ አዋጭ ቢዝነሶችን የማማከር ሥራን እንደሚሰሩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሊያቋቁመው ነው የተባለው የኢንቨስትመንት ባንክ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችና ኩባንያዎች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ በሚቀላቀሉበት ጊዜ የማማከርን ሥራ ለመስራት ያለመ መሆኑን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ሃይለመስቀል ተናግረዋል።

ቀደም ባሉ ጊዜያቶች በነበረው ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦባቸው የቆዩ ኢንደስትሪ ፓርኮች እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

ሆኖም አሁን ላይ ባለው የኢኮኖሚ መነቃቃት የተነሳም ከ10 በላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውን የመንግሥት ሪፖርት ያስረዳል።