ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች ባለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ቅርሶች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲል፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የቅርስ ምዝገባ ጥናት ደረጃ ምደባና ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበራ አንጀሎ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አንዳንድ አካባቢዎች ቅርሶች በሚመቹ ቦታዎች ላይ አለመኖራቸውን አንስተው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ሰላም አለመኖሩ በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ቅርሶች ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል እና ተጋላጭ ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡
አክለውም አሁን ላይ ባለው የቅርብ ጊዜ መረጃ ቅርሶች ላይ በግልፅ 'ይህ ነው' የሚባል የደረሰ ጉዳት ባይኖርም፤ ስጋት በመኖሩን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የቅርሶችን ይዞታና ደህንነት በተመለከተ በአዋጁ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ሊያሳውቅ የሚገባው በቅርብ ያለ አካል እንደሆነ ገልጸው፤ "ጥያቄ ከቀረበ ግን አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኙ ቅርሶች ተመዝግበውና ታውቀው ዲጂታል በሆነ መንገድ የተቀመጡ ባለመሆናቸው፤ ለሕገ-ወጥ ዝውውር ተጋላጭ መሆናቸውን አቶ አበራ ገልጸዋል።
መሪ ሥራ አስፈፃሚው ግንዛቤን የመፍጠር ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በቅርቡ የዓለም አቀፉ ሕገወጥ ቅርስ ዝውውር መከላከል ቀንን ምክንያት በማድረግ አክሱም ላይ በመሄድ ከጦርነቱ በኋላ ቅርሶች በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ውይይት ማካሄዱን አስታውሰዋል።
በዚህም "አንዳንድ ቅርሶች ለሕገወጥ ዝውውር ተጋላጭ መሆናቸውን አይተናል" ብለዋል።
በሕገወጥ የተመዘገበ ቅርስ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተያዘ ወይም 'ከነበረበት ቦታ ጠፍቷል' ተብሎ ያቀረቡት አካል እንደሌለ ገልጸው፤ ነገር ግን ሕገወጥ ዝውውር እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተዘረጋና ውስብስብ አሰራር ያለው በመሆኑ ሁሉም ሰው የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ ቅርሶቹን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶች አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ
ሕገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን ሁሉም ሊያስቆመው እንደሚገባ ተጠቁሟል