ታሕሳስ 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የያዛቸውን የከተማ ቦታዎች ለማልማት ጥረቶች ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፤ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የተሳካ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን አስታውቋል።

"በዚህም የተነሳ ቦታዎቹ በከተማ አስተዳደሮች ዓይን ውስጥ እየገቡ እና የመነጠቅ ሁኔታዎች እያጋጠሟቸው ይገኛል" ብሏል።

ለአብነትም በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኝ የአበራ ጋሙ ማሰልጠኛ ማዕከል ግቢ 40 ሺሕ ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታ ከአልሚዎች ጋር በመሆን ለማልማት ዲዛይን ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ መደረጉን ገልጿል።

"ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ምትክ ቦታ ሳይሰጥ አብዛኛውን ቦታ ወስዶ፤ ለነዋሪዎች በማከፋፈል መኖሪያ ቤቶች ተገንብተውበታል" ያለው ኮንፌዴሬሽኑ፤ "አሁንም ቢሆን 10 ሺሕ ካሬ ሜትር የሚሆን የቀረ ቦታ ቢኖርም፤ መገንባት ካልተቻለ ከፍተኛ ስጋት ተደቅኖበታል" ሲል አስታውቋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተወሰደበት ቦታን ምትክ የከተማ አስተዳደሩ ቃል በገባው መሠረት ለኮንፌዴሬሽኑ መስጠቱን ገልጿል።

በዚህም "ከሁለት ዓመት በፊት ለልማት የተወሰደውን ፍራንክ አዲስ የሚባል ሬስቶራንት ይሰራበታል ተብሎ የነበረውን ቦታ ምትክ ጨምሮ፤ 3 ሺሕ 495 ካሬ ሜትር ተሰጥቶኛል" ብሏል።

ሆኖም በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ግንባታ ካልተሰራበት ስጋት ውስጥ የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልጿል።

አባል ሠራተኞች እና ማህበራት እነዚህን ቦታዎች ለማልማት የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ ሊተባበሩ እንደሚገባም የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ጥሪውን አቅርቧል።