ታሕሳስ 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ በቱርክ አንካራ ከሶማሊያ ጋር ያደረገው ስምምነት፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የፀጥታ እና የሰላም እጦት አንጻር ምን አልባት የውስጥ ችግሯ ላይ እንድታተኩር ይረዳት እንደሆነ እንጂ፤ በሚፈለገው ልክ ጥቅሟን እና መብቷን የሚያስጠብቅ ስምምነት ነው ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም ሲሉ የጂ-ኦ ፖለቲካ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
አሐዱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህር በር የማግኘት መብት አላት ከሚለው ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌ በመነሳት፤ "የአዲስ አበባ እና የሞቃዲሾ የዲፕሎማሲ ስምምነት እጣ ፋንታው ምን ሊሆን ይችላል" ሲል ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡
ባለሙያዎቹ በምላሻቸው፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምንም አይነት እውቅና ከሌላት ሀገር ሶማሊያላንድ መንግሥት ጋር ያደረገውን ስምምነት ጋብ በማድረግ፤ ከሶማሊያ ሉዓላዊ መንግሥት ጋር ንግግር ማድረጉ አውንታዊ ነው" ሲሉ አድንቀዋል፡፡
"ነገር ግን ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በቀጠናው የገጠማትን ውጥረት በማርገብ፤ የውስጥ ችግሯ ላይ እንድታተኩር ስለሚረዳት፤ መንግሥት የሄደበት መንገድ የዲፕሎማሲ ጥበብ ነው" ሲሉ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የኢኮኖሚክስ ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አክለውም "ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከሶማሊያ ጋር ሊያስገባት ተደቅኖ የነበረውን ውጥረት ማስቀረት ችላለች" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችው ስምምነት በቀጠናው የገባችበትን ውጥረት እንደሚያረግብ ያስረዱት ደግሞ ሌላኛው የዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና መምህሩ ዶ/ር ደጉ አስረስ ናቸው፡፡
"ነገር ግን ኢትዮጵያ መብት እና ጥቅሟን የምታስከብርበት መንገድ መጀመሪያ ከጎረቤት ጋር ሰላም ስትፈጠረ ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"ነገር ግን አሁን ባለችበት ሁኔታ የባህር በር የማግኘት ተስፋ የለውም፡፡ በቀጣይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲዋን ማስተካከል የምትችል ከሆነ፤ መብት እና ጥቅሟን እንድታስከብር ያስችላታል" ሲሉ ደ/ር ደጉ አስረስ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል፡፡
አሐዱ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አክለውም፤ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚታዩ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በትኩረት ማጤን አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተያያዘ በትናንትናው ዕለት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ጉብኝቱ በአንካራው ስምምነት መሰረት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲል የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።