የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የከተማ ቦታዎች ለሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እየተጋለጡ መሆኑን፤ የክልሉ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ችግሩን ያባባሰው የከተማ መሬትን በሊዝ ለማስተላለፍ የወጣው አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጉ እንደሆነ ቢሮው ገልጿል።
የክልሉ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ደርበው ዘንቶ፤ ስልጣን ያለው አካልም ቢሆን ሕጋዊ አሰራርን ያለመከተል ችግሮች እንዳሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ "ለሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ከተጋለጡት መካከል የመንግሥት ይዞታዎች እና የሕዝብ የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎች ይገኙበታል" ብለዋል፡፡
ማንኛውም የመሬት ፍላጎት ያለው አካል በሕጋዊ መንገድ ብቻ የሚገባውን ማግኘት ሲገባው፤ በሕገ-ወጥ መንገድ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ፈፃሚና አስፈጻሚ አካላትም የአዋጁን መሰረታዊ ድንጋጌዎች በመረዳት እና የሕግ ተጠያቂነት ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በቤንሻንጉል ክልል የከተማ ቦታዎች ለሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እየተጋለጡ መሆኑ ተገለጸ
