የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ጎንደር ዩንቨርስቲ ለሚመጡ ተማሪዎች የሚደረገው ልዩ አቀባበል፣ የቃል ኪዳን ቤተሰብ የማስተዋቅና የማስተሳሰር መርሃ ግብር፤ በሰላም ሚኒስትር እውቅና ሊሰጠው ይገባል ሲሉ የከተማዋ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኜው ጠይቀዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ "የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት" በሚል ስያሜ ከ2012 ዓ.ም የጀመረውና ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ያዘጋጀው "የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር" መርሃ ግብር፤ በዛሬው ዕለት በዩንቨርስቲው በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል።

በዚህም መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኜው፤ "የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት የጀመረው ይህ መርሃ ግብር፤ በሌሎች አካባቢዎች እና በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እንዲሰፋና እንደ ምርጥ ተሞክሮ እንዲታይ በሰላም ሚኒስትር በኩል ለሰላሙ ዩኒቨርሲቲ እውቅና ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል፡፡

Post image

"የሰላም አንዱ መንገድ መዛመድ እና መተዋወቅ ነው" ያሉት ተቀዳሚ ም/ከንቲባው፤ ይህም ትስስርና ቤተሰባዊ ግንኙነት አንዳችን ለሌላችን ያለንን ትስስር ያዳብረዋል፣ ያጎለብተዋልም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 'የሰላም ዩኒቨርሲቲ' የሚለውን ሥም ለመጠሪያነት ብቻ የሚጠቀመው አይደለም፡፡ በተጨባጭም ሰላም ምልክቱ እና እሴቱ ነው" ያሉም ሲሆን፤ ሰላም ሚኒስቴር ይህንን በልዩ ሁኔታ ይረዳዋል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

"ጎንደር በታሪኳ እንዳስመሰከረችው ተከታታይ የብዙ መቶ ዓመታት የአብነት ትምህርት ለመማር ሊቃውንቱን ብለው የሚመጡ ተማሪዎች ቀለብ ጭነው አይመጡም" ያሉት ተቀዳሚ ም/ከንቲባው፤ "ጎንደር አስተምራ፣ ተንክባክባና ለሊቃውንትነት አብቅታ ትሸኛቸዋለች፡፡ ይህ በደረሳ እስላማዊ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ የተረጋገጠ ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም ሂደት ውስጥ ከተማዋ በርካታ ታላላቆች ሰዎችን ለማፍራት መቻሏን አስረድተዋል፡፡

Post image

"ጎንደር ዩኒቨርስቲ የጀመረው የቃል ኪዳን ቤተሰብ አዲስ መንገድ፤ ከነበረው የተቀዳ ሀገር ሊማርበት እና ሊስፋፋ የሚገባው ተሞክሮ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሀሳቡን ላፈለቁት ለቀድሞ የከተማዋ ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም፣ ሀሳቡን ተቀብሎ ወደዚህ ላደረሰው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር እንዲሁም ሀሳቡ እውን እንዲሆን ቁርጠኝነት ላሳየው የከተማዋ ነዋሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም "ዛሬ በዚህ ሥርዓት የቃል ኪዳን ቤተሰባዊ ትስስር የምትፈጥሩ ተማሪዎችና ቤተሰቦች በታሪካዊቷ ከተማ ታሪክ እየሰራችሁ ስለሆነ ልትኮሩ ይገባል" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የከተማዋ ታላላቅ አባቶች አቶ ባዩ በዛብህ እና ሀጂ ማሩፍ የተገኙ ሲሆን፤ አቶ ባዩ ባስተላለፉት መልዕክት "ዩንቨርስቲው ይሄን መርሃ ግብር ማዘጋጀቱና ማስተባበሩ ተማሪዎችን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን የሀገር አንድነትንም ለማጠናከር የሚያደርገውን ብርቱ ጥረት ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡

Post image

በመሆኑም "በተለይ የሰላም ሚኒስቴር ይሄን ጉዳይ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በማቅረብ በጀት እንዲወሰንለት ሊያደርግ ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሀጂ ማሩፍ በበኩላቸው "ጎንደር ሰላም ፈላጊ፣ የሰላም መስራች ሀገር ነው" ያሉ ሲሆን፤ መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት ዩንቨርስቲው ሰላምን፣ ፍቅርን እና አብሮነትን ለማስፋፋት እየሰራው ላለው ሥራ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Post image

በተጨማሪም ስለ"ጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ" ምስክርነት ለመስጠት ከሀዋሳ፣ ከወልቂጤ፣ ከአዳማ እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የቃል ኪዳን ተማሪዎች ወላጆች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በዚህም ምስክርነታቸው የቃል-ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር መርሃ ግብር በሕዝቦች መካከል የነበረው የተዛባ አመለካከት የቀየረና ያለውን የኢትዮጵያዊ መንፈስ እና አንድነት እያጠናከሩ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ እንደወላጅ ይሰማቸው የነበረውን ስጋት ያቃለለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ