ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዛሬ ለሊት 10 ሰዓት ከ46 ላይ በሬክተር 4 ነጥብ 9 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን አካባቢ መከሰቱን የጀርመን የጂኦሳይንስ ጥናትና ምርምር ማዕከል (GFZ) መረጃ አመላክቷል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከመሬት በታች 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ የተከሰተ መሆኑም በመረጃው ተገልጿል።
የዚህም የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በበርካታ የአዲስ አበባ ከተሞች ላይ ለረጅም ሰከንዶች የተሰማ ሲሆን፤ በመገናኛ፣ ቀበና፣ ጎሮ፣ አያት 49፣ ጣፎ፣ ጀሞ፣ ኮዬ ፈጬ፣ አስኮ፣ ቀበና እንዲሁም በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች ንዝረቱ መሰማቱን አሐዱ ከየአካባቢዎቹ ምንጮች ያገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ከአዋሽ 5 ነጥብ 7ኪ.ሜ ደቡባዊ አቅጣጫ ላይ በሬክተር 4 ነጥብ 7 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ትናንት ከምሽቱ 5:24 ደቂቃ አካባቢ የተሰማ ሲሆን፤ ይህም ከመሬት በታች 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ የተከሰተ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የአፋር ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች እየተስተዋሉ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ክስተቶቹ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ ከማጣላቸው በተጨማሪ በመኖሪያ ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች እና መንገዶችን ጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ተመስገን ጥሩነህ ከሰሞኑ በተከታይ እየተከሰቱ የሚገኙ የርዕደ መሬት ክስተቶች ምላሽ እና ቅድመ ማስጠንቀቅ ዙሪያ በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተሰራ መሆኑን በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
በመልዕክታቸውም "የርዕደ መሬት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጁነታችንና የምላሽ ሁኔታችን ባለን ቴክኖሎጂ፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ትንተናና የትንበያ አቅም የሚወሰን ነው፡፡" ያሉ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ የስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ባደረጉት ጉብኝት በርዕደ መሬት ነክ ሳይንሳዊ ምርምር አበረታች ሥራዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የሳይንሳዊ ትንተና እና ትንበያ ቡድኖችን በማደራጀት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።