ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 1:30 ገደማ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ከዚህ በፊት ያልተለመደ ተቀጣጣይ እሳት መሰል ነገር በሰማይ ላይ መታየቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጉጂ፣ በዱራሜ፣ በጋምቤላ፣ በቡሌ ሆራ፣ በኮንሶ፣ በቡርጂ፣ በሆሳዕና እና በኦሞ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ምሽቱን በሰማይ ላይ የታየው ተምዘግዛጊ ሮኬት መሳይ ተቀጣጣይ ነገር ምንነቱ እስካሁን ባይታወቅም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በክስተቱ መደናገጣቸውን ተናግረዋል።

Post image

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ክስተቱን በምስል እና በተንቀሳቃሽ ምስል አስቀርተው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያጋሩት ሲሆን፤ ተቀጣጣይ ብርሃናማ ነገሩ በኢትዮጵያ አልፎ በኬንያ ሰሜናዊ ምስራቅ አካባቢዎች እንዲሁም በኬንያ ሞያሌ በክብ መታየቱ ታውቋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሰማይ ላይ እየተቀጣጠሉ በከፍተኛ ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቁስ አካላት ስብስብ መታየታቸው ሪፖርት እንደደረሰው ዛሬ ጥዋት አስታውቋል።

ተቋሙ "በደረሰን ተንቀሳቃሽ ምስል ለመመልከት እንደቻልነው የእነዚህ አካላት ስብስብ የጠፈር ፍርስራሾች አልያም የሚቲዮር አለቶች ይመስላሉ" ያለ ሲሆን፤ "ስብስቡ ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት በሰማይ ላይ ሲምዘገዘግ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል" ሲልም ገልጿል።

የክስተቱን ተፈጥሮ በእርግጠኝነት ለማብራራት ያስችል ዘንድ ሁኔታውን በቅርበት እያጣራው እንደሚገኝ የገለጸም ሲሆን ፤ ወቅታዊ መረጃዎችን እንደደረሱት ይፉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ተቋሙ የማጣራት ሥራ እንኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ሰው በተረጋጋ መንፈስ እንዲጠባበቅም ጥሪውን አቅርቧል።

ቀናቶች በፊት የጠፈር ስብርባሪ ኬንያ ውስጥ ባለ አንድ ገጠራማ ቦታ ላይ መውደቁ ይታወሳል።