ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ መንገድ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እንዲሁም መስመር ማቆራረጥ ድርጊቶችን በሚፈፅሙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ የቁጥጥር ስርዓቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በማንኛውም ቦታ እና በየትኛውም ጊዜ ከተቀመጠለት ሕጋዊ ታሪፍ በላይ ባለመክፈል ኅብረተሰቡም መብቱን እንዲያስከብር እና ሕገ-ወጥ የሚፈፅሙ ተሽከርካሪዎችን ሰሌዳና ኮድ ቁጥር፣ ሰዓትና ቦታ በመግለፅ ለቢሮው ጥቆማ በመስጠት የሚደረገውን የቁጥጥር ስርዓት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል።
የትራንስፖርት ቢሮው በከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ያለምንም ታሪፍ ጭማሪ፤ በመደበኛው ታሪፍ መሰረት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
ኅብረተሰቡ ለትራንስፖርት ጉዳይ ጥቆማ ለመስጠት በነፃ የስልክ ጥሪ መስመር በ9417 እንዲጠቀምም ቢሮው ጠይቋል።