ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከተወለዱ ከመጀመሪያው ቀናቸው እስከ ሰባት ቀን አመት በታች ከሆኑ፤ ከአንድ ሺሕ ጨቅላ ሕጻናት ውስጥ 33 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጽንስ ጊዜ የምግብና የአየር መቆራረጥ፣ የነርቭ ዘንግ ክፍተት፣ በወሊድ ጊዜ የጨቅላ ሕጻናት መታፈንና ከክብደት መጠን በታች ሆኖ መወለድ ለሕጻናቱ ሞት መንስኤ መሆኑን፤ በሚኒስቴሩ የጨቅላ ሕጻናት እና ሕጻናት ጤና ዴስክ አስተባባሪ መለስ ሰለሞን ለአሐዱ ተናግረዋል።
እንዲሁም በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት ለሕጻናቱ ሞት አንዱ መንስኤ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፤ በጨቅላነት ወቅት ለሚከሰት ሞት ደግሞ በወሊድ ወቅት ከሚከሰት የመታፈን ችግር ጋር ተያይዞ በጀርም መመረዝና የሳንባ ምች ለሞት የሚዳርጉ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
የችግሩን ግዝፈት በመረዳት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለችግሮቹ የሚወሰዱ መፍትሄዎችን በተመለከተ ከቀበሌ እስከ ከተሞች እናቶች ቅድመ እርግዝና ክትትል እና ቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም፤ በእርግዝና ወቅት ያለ የአመጋገብ ስርዓት ማስተካከል እንደሚገባቸው ግንዛቤ የማጨበጥ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሞት ምጣኔው በፈረንጆቹ በ2019 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር መሻሻል ያሳየ ቢሆንም፤ "አሁንም በተለይ የጨቅላ ሕጻናት ሞት ላይ መሰራት አለበት" ብለዋል።
አያይዘውም በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት እታዩ ያሉ ለውጦችን ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች በቅንጅታዊ መልኩ እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በተለያዩ የሚዲያ አግባቦች በመጠቀም ለሕብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን በቀጣይነት ለመቅረፍ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ