ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኔዘርላንድ በፍቃደኝነት ወደ ደማስቆ ለሚመለሱ እና ተመልሰው ለማይመጡ ስደተኞች በመደበኛነት ከሚሰጠው 500 ዩሮ ወደእጥፍ የሚጠጋ ክፍያ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡

የኔዘርላንድ የጥገኝነት አስፈጻሚ ሚኒስትር ማርጆሊን ፌበር፤ የአምባገነኑ በሽር አል አሳድ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ወደ ሶሪያ መመለስ የሚፈልጉ የሶሪያ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ካቋረጡ 900 ዩሮ በጥሬ ገንዘብ እና ለደማስቆ ትኬት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

ክፍያው በኔዘርላንድ በሕገወጥ መንገድ ላሉ፣ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ላላቸው ወይም ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ላሉ ሶሪያውያን ሲሆን፤ ስደተኞቹ በምትኩ ማንኛውንም የመኖሪያ ፈቃድ ወይም የወደፊት የጥገኝነት ጥያቄን በቋሚነት የሚሰርዝ ሰነድ መፈረም አለባቸው ተብሏል።

የስደት ተመላሽ እና ሰፈራ አገልግሎት የአሳድ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ ሶርያውያን ወደሀገራቸው ለመመለስ ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጿል፡፡

አገልግሎቱ መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞችን ለመርዳት ልዩ ዌብሳይት ማበልጸጉንም አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 160 ሺሕ ሶርያውያን በኔዘርላንድ ይኖራሉ የተባለ ሲሆን፤ ሀገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2023 ወደ 27 ሺሕ የሚጠጉ ስደተኞች ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥታለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሶሪያ ዜጎች መሆናቸው ተነግሯል።

እ.ኤ.አ. በ2022 በ3,000 ሶሪያውያን ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ አብዛኞቹ በአገራቸው ያለው ሁኔታ ካልተሻሻለ መመለስ አይፈልጉም።

አሁን ላይ የኔዘርላንድ መንግሥት ለስደተኞቹ "የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ካቋረጡ እሰጣለሁ" ያለው ገንዘብ እና የአየር ትኬት ስደተኞቹ ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የበረታታል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ