ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሽጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ ያለው እንዲሁም፤ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም የነዳጅ መሸጫ ዋጋው በእጅጉ ያነሰ ነው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "እንደ ዓለም አቀፉ የፔትሮል ዋጋ መረጃ የጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1.25 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡" ብለዋል፡፡
"ይህ የሚያመለክተው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሽጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑን ነው፡፡" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም ካየነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ምሳሌም በኬንያ 1.351፣ በሩዋንዳ 1.136፣ በኡጋንዳ 1.299፣ በታንዛንያ 1.127 የአሜሪካን ዶላር በሊትር በተመሳሳይ ወቅት እየተሸጠ እንደሚገኝ ያነሱ ሲሆን፤ "እጅግ ደሃ በሚባሉት እንደ ማላዊ በ1.459፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብልክ 1.746 የአሜሪካን ዶላር በሊትር እየተሸጠ ይገኛል" ብለዋል፡፡
አክለውም በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነዳጅ በሊትር ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
"እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባራቸው ተጠምደዋል።" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "እነሱ የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም። ራሳቸውን ለሕዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለሕዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉ። ይህን የሚያደርጉት እዉነታዉን ስለማያዉቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንደይገለጥ ነዉ።" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም 'አንዳንድ ወገኖች' ያሏቸው አካላት ተሳስተዉ እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለዉ በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በህብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡ "ለምን ቢባል ይህ ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጣራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡ እነሱ ይህ የላቸዉም፡፡" ብለዋል፡፡
"በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቻዉ አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጣል እኩይ ፍላጎታቸዉን ማሳካት ነዉ፡፡ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነዉ፡፡ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግሥት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም ነው።" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"በነጻ ገበያ ውስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ስርዓት መንግሥት እንዲያደርግ የማይገደድባቸዉ ጉደዮችን በማንሳት መንግሥትን ይከሳሉ፡፡" ያሉም ሲሆን፤ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት እንደማይወስድ ገልጸዋል።
"መንግሥት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል። በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል።" ያሉም ሲሆን፤ ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የህብረሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ እንደሚሰራና ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም እንደሚረዳ ገልጸዋል።
"በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድሃኒትና መሰል የጤና ጉዳዮች ወዘተ ከፍተኛ የሚባለውን ድጎማ እያደረገ ነው። በዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ያደርጋል። መንግሥት መደበኛ ተግበራትንም ያከናውናል።" ብለዋል፡፡
"ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ ነው።" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽለ፣ ገብስ፣ ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም "የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው።" ያሉም ሲሆን፤ የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ሥራም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም ሕዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን በቅርቡ በሚንስትሮች ደረጃ በሁሉም ክልሎች የተደረገው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን መረጋገጡን አብራርተዋል።
"መንግሥት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው።" ያሉም ሲሆን፤ እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም "አጋጠሚውን በመጠቀም ህብረተሰቡ ላይ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጃ ይወስዳል፡፡" ሲሉ ተናግረዋል፡፡