ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በሚገኘዉ የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ንዑስ ቅርንጫፍ፤ የሩሲያ መንግሥት ጋምቤላ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች አንድ ሺሕ 632 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ "የሩሲያ ሕዝቦች ለኢትዮጵያ ሕዝብ" በሚል የተደረገ ሲሆን፤ እርዳታውን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ለሆኑት ጀኒፈር ቢቶንዴ አስረክበዋል።

Post image

ሩሲያ ያደረገችው ድጋፍ በጋምቤላ ለሚኖሩ ከ163 ሺሕ በላይ አባወራዎች የሚውል ሲሆን፤ የሩሲያው አምባሳደር "እርዳታው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የልማት ትብብርና አጠቃላይ የሁለትዮሽ ግንኙነት አካል ነው" ብለዋል።

በቀጣይም የሩሲያ መንግሥት ለኢትዮጵያ መሰል ሰብአዊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ አክለዉም ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ወንድማማችነት ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት፤ በ80ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት “ከባድ ረሃብ” እየተባለ በሚጠራው ወቅት ኢትዮጵያን በአውሮፕላን፣ በሄሊኮፕተርና በጭነት መኪናዎች የሰብዓዊ አቅርቦቶችን በማጓጓዝ እርዳታ ማድረጓን ገልጸዋል።

Post image

"ይህን የወዳጅነት ባህላችንን ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የመስጠት እንቀጥላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚደረገዉ የሩስያ እህል አቅርቦት በጋምቤላ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞችን ለመደገፍ ይረዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል።