መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰት ድርቅ በዝርያዎች ላይ የመጥፋት አደጋ መደቀኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሚያከናውነው የምርምር የሥራ ሂደት መሠረት በምግብ ዝርያዎች በተለይም በገብስ፣ ማሽላ እና በቆሎ ላይ የመመናመን ሁኔታ ስለመታየቱ የገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከእንስሳት ዝርያ ደግም በዋልያ ላይ የመመናመን ሁኔታ መኖሩን አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በምግብ እና በእንስሳት ዝርያዎች ላይ የምርምር ሥራ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት የኢንስቲትዩቱ መሪ ሥራ አስፈጻም አቶ ውብሸት ተሾመ፤ እንደ አጠቃላይ በዝርያዎች ላይ ያለውን የመጥፋት አደጋ በተመለከተ ጥናት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የሚከናወነው የምርምር ሥራ ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሠራ የገለጹም ሲሆን፤ በጥናቱ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ዝርያዎች መልሶ የመተካት ሥራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል፡፡

አክለውም የመጥፋት አደጋ የተከሰተባቸውን ዝርያዎች በአንድ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ እንደማይገኙ በማንሳት፤ በአንጻሩ በሌላ አካባቢ ዝርያው የሚገኝበት ሁኔታ በመኖሩ ዝርያዎቹ እንደ ሀገር ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

በድርቅ ምክንያት ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ እና እንዲሰደዱ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር በዝርያዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳትን እያስከተለ እንደሚገኝ ይገለጻል፡፡

በአየር ንብርት ለውጥ ምክንያት መጤ ወራሪ ዝርያዎች በነባር ዝርያዎች ላይ ጉዳት እያስከተሉ እና ለመጥፋት አደጋ መነሻ ምክንያት ስለመሆናቸው መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ውብሸት ገልጸዋል፡፡

የዘርፉ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከዛሬ 45 ዓመት በፊት በኢንቲትዩቱ የተሰበሰቡ ዝርያዎች ስለመኖራቸው የተናገሩ ሲሆን፤ ያሉት ዝርያዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የመጥፋት አደጋዎች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን አቅም የማጥናት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አክለውም አርሶ አደሩ በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀመበት የሚገኙ ዝርያዎች ጥሩ ምርት የሚያስገኙበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፤ በዝርያዎቹ ላይ ግን በጊዜ ብዛት የመዳከም ሁኔታ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ