ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ባለፉት 6 ወራት 144 የእሳት እና 100 ሌሎች አደጋዎች በድምሩ 244 አደጋዎች መከሰታቸውን፤ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
በዚህም ምክንያት የ46 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በ81 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል አደጋ መድረሱን እንዲሁም፤ ከ370 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል።
በተጨማሪም 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ከአደጋ ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ በአደጋ ውስጥ የነበሩ 19 ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉንም አቶ ንጋቱ ገልጸዋል።
"የተከሰቱት አደጋዎች ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀሩ የዚህ ዓመቱ ጭማሪ አሳይቷል" ያሉት ባለሙያው፤ የአደጋዎቹ መንስኤ የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከደረሱት 244 አደጋዎች መካከል 27ቱ አደጋዎች የደረሱት በሸገር ከተማ ሲሆን፤ በቦሌ ክፍለ-ከተማ 35፣ በየካ 27፣ በአዲስ ከተማ 25፣ በልደታ ክፍለ-ከተማ 12 አደጋዎች ባለፉት 6 ወራት ማጋጠሙንም ገልጸዋል።
በእመቤት ሲሳይ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ባለፉት 6 ወራት ባጋጠሙ 244 የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት የ46 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ
በአደጋዎቹ ከ370 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል