ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተገልጋዮች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ከሚነሳባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፤ ደላሎች አገልግሎት ፈላጊውን እያንገላቱ የቅሬታው ምንጭ ሆነዋል ሲል ገልጿል፡፡
የአገልገሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ይህንን በሚመለከት እንደተናገሩት፤ በአገልግሎቱ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ከካቻምና፣ አምና ከአምና ደግሞ ዘንድሮ እየቀነሱ ይገኛሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት፤ ዓመቱ ሳይጠናቀቅ የተሰጠው የፓስፖርት መጠን ከአምና ጋር ብቻ እንኳን ሲነፃፃር በዓመቱ ሙሉ ከተሰጠው በመብለጡ ነው፡፡
"በባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ፓስፓርት ተሰርቶ ተሰጥቶ ነበር" ያሉ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን በስድስት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓስፖርት እጃቸው ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ721 ሺሕ በላይ የተለያዩ ፓስፖርት ተዘጋጅቶ ለዜጎች መሰራጨቱን ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡
"በመሆኑም የነበረውን ነባር የፓስፓርት አስጣጥ ሂደት ለመቀየር ወደ ዲጂታል መንገድ መምጣት ግድ በመሆኑ ይህንን መንገድ እየተከተልን ነው" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ እየተሰራና ፓስፓርት እየተሰጠ የነበረው በነባሩ ሲስተም በመሆኑ፤ ሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩ እንዳልቀረም ያነሳሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ በር ላይ ጀምሮ ጥበቆች እና ደላላችም ጭምር አገልግሎት ፈላጊውን በከፍተኛ መጠን እያንገላቱት የቅሬታ ምንጭ እየሆኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ይህን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ያነሱት ሰላማዊት ዳዊት፤ ለዚህ መፍትሄው ወደ ዲጂታል ፓስፓርት መምጣት አምራጭ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"የሚቀጣውን እየቀጣን ዲጂታል መንገዱን ማስፋት እንዲሁም፤ የቀድሞውን ሲስተም በማስቀረት ወደ አዲስ መንገድ የማሰገባት ሥራ እንሰራለን" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከፓስፓርት እና ሌሎች አገልግሎቶች 10 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ በእቅድ ተይዞ 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለጸ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 79 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በውጭ ምንዛሬ የተሰበሰበ መሆኑንን አስታውቋል፡፡
ደላሎች አገልግሎት ፈላጊውን እያንገላቱ የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል ሲል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ
አገልግሎቱ በ6 ወራት ውስጥ 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል