ታሕሳስ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ጦርነቱ መቆሙ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እየረገቡ መምጣታቸው ቢነገርም ተፈናቃዮች ወደቀደመ ስፍራቸው አለመመለሳቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ተፈናቃዮቹ በሚገኙባቸው መጠለያ ካምፖች በቂ ድጋፍ አለማግኘት፣ ለበሽታ ተጋላጭነት በአንድ አንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ስጋት ውስጥ መግባታቸውም ሲገለጽ ቆይቷል።

አሐዱም "በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?" ሲል ጠይቋል።

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉና በአበይ አዲ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይ፤ ቀድሞ የሚደረግላቸው ድጋፍ አጥጋቢ እንዳልነበር የገለጹ ሲሆን፤ ለበዓልም ቢሆን ምንም አይነት ድጋፍ አለመደረጉን ገልጸዋል።

"ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተቻላቸው መጠን ድጋፍ ያደርጉልናል" ያሉት ተፈናቃዩ፤ "የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከእኛ ጉዳይ ይልቅ የስልጣን ሽኩቻ ላይ በመጠመዱ ረስቶናል። በዚህም ተስፋ ቆርጠናል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ሌላው አሐዱ ያነጋገራቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃይ ሐምሌ ላይ በአካባቢው ነዋሪዎችና በታጣቂዎች መካከል 'መሳሪያ አስረክቡ' በሚል ተፈጠረ በተባለ ግጭት ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን ላለፉት ስድስት ወራት አንድ ጊዜ ብቻ እርዳታ እንደተደረገላቸው ገለጸው፤ አሁን አካባቢው ላይ የመከላከያ ሰራዊት መግባቱን አንስተዋል።

"በቅድሚያ ሰላማችንን ነው የምንፈልገው" ያሉት እኚሁ ተፈናቃይ፤ ህብርተሰቡ የከፋ ችግር ውስጥ ስለመሆኑንም ጠቁመዋል።

Post image

ከወለጋና ምሥራቅ ሸዋ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን በሦስት የመጠለያ ጣቢያዎ የሚገኙ ተፈናቃዮች አስተባባሪ በበኩላቸው፤ "ለተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ በቋሚነት አይደረግም" ያሉ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ ቆይቶ በቅርቡ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

አክለውም በበዓል ሰሞን ከአካባቢው ነዋሪም ሆነ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተደረገ ድጋፍ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም በቋሚነት የነበሩ ግብረ ሰናይ ተቋማት ጊዜያቸው እያጠናቀቁ በመውጣት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት "ለከፋ ችግሮች ተጋልጠናል" ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት የየአካባቢዎቹ ተፈናቃዮች፤ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው እንዲሁም ችግሮች በዘላቂነት ተፈተው ወደቀደመ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በግንቦት ወር 2024 ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት በግጭትና ጦርነት፣ 500 ሺሕ የሚሆኑት በድርቅ ቀሪዎች ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ እና በልማት ሥራዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ማስታወቁን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።

ከእነዚህም ውስጥ 56 ከመቶ የሚሆኑት ከ1 ዓመት፣ 23 ከመቶ የሚሆኑት ከ2 እስከ 4 ዓመት እና 11 ከመቶ የሚሆኑት ከ5 ዓመት በላይ በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በሪፖርቱ አመላክቷል።