ታሕሳስ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሥም የነበራቸው አንጋፋው የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በማረፋቸው የተሰማኝን ኀዘን እገልጻለሁ" ብለዋል።
አክለውም፤ "በሚችሉት ሁሉ ሀገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑትን የትምና መቼም የሚናገሩ ነበሩ" ሲሉ ገልጸዋል።
"እንዲህ ዓይነት ብርቱ ሽማግሌዎችን ማጣት ጉዳቱ ለሀገር ነው። ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይቀበላት" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በ1923 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ የተወለዱት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን ሰርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥረው በተለያዩ ሀገራት አገልግለዋል።
አቶ ቡልቻ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መስራች የነበሩም ሲሆን፤ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጅግ ጠንካራ ቃላትን ፈገግታን በሚያጭሩ ቀልዶች አጅበው በድፍረት በመናገር ይታወቃሉ፡፡
ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት ታህሳስ 28/04/17 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።