የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጣና አሽከርካሪዎች ማህበር በትንሹ 20 የሚጠጉ ኬላዎች ላይ አሽከርካሪዎች ክፍያ እየተጠየቁ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን ለአሐዱ ገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ካሳሁን ጎፌ በሀገሪቱ በአጠቃላይ ከ280 በላይ ሕገ-ወጥ ኬላዎች መኖራቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የጣና አሽከርካሪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ሰጡ ብርሃን ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "የመንግሥት አካላት ችግሮችን ማሳየት እና መናገር ሳይሆን የመፍትሄ አካል መሆን አለባቸው" ብለዋል፡፡
መንግሥት የመዋቅር ትስስሩን በመጠቀም ሕገ-ወጥ ኬላዎችን የማፍረስ ሥራውን መስራት አለበት እንጂ፤ ችግሩ እንዳለ መጠቆም ብቻውን ተገቢ ምላሽ አይደለም" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በየቦታው 'ለልማት እና ለተለያዩ ወጪዎች' በማለት ኬላዎችን እያለፉ ሌሎች ሥራዎችን እየተሰሩ እንደሚገኙ የሚገልጹት ዋና ጸሀፊው፤ "አንድ ሹፌር በአንድ መንገድ 20 በላይ ደርሰኝ እየተቆረጠለት ነው የሚያልፈው" ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ተናግረዋል፡፡
"የትራንስፖርት ዘርፉ ሊጠበቅ የሚገባው ቢሆንም፤ ይህን ግን የሚመለከተው አካል የሚገባውን ጥበቃ እያደረገለት አለመሆኑን የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ሹፌሮች እንኳን ችግሩን ተቋቁመው ለመስራት ቢሞክሩም ይህ ሁኔታ ዳፋው ማህበረሰቡ ላይ የወረደ በመሆኑ ችግሩን የከፋ ያደረገዋል ሲሉ አቶ ሰጡ ተናግረዋል፡፡
ከኬላ ጋር በተያያዘ በርካታ አቅጣጫዎች በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ እንዲሁም በጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ላይ ወሳኔ እንደሚወሰድ የተገለጸ መሆኑን በማንሳት መፍትሄ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
አሐዱም ጉዳዩን አስመልክቶ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴርን የጠየቀ ሲሆን፤ ከሚኒስቴሩ ኮምኒኬሽን ባገኘነው መረጃ መሰረት ይህ ሀሳብ የተቋሙ መሆኑን ገልጾልናል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ከሰሞኑ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሀገሪቱ ባሉ ሕገወጥ ኬላዎች ላይ እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ የሚቀበሉ መኖራቸውን ገልጸው፤ በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመላ ሀገሪቱ ሕገ-ወጥ ኬላዎች መኖራቸውን በማንሳት፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም አካላት ትብብር እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አሽከርካሪዎች በአንድ ጉዞ ከ20 በላይ ኬላዎች ላይ ክፍያ እየተጠየቁ ነው ሲል ጣና አሽከርካሪዎች ማህበር አስታወቀ
