የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶችን አጠቃሎ የያዘ የሞባይል መተግበሪያ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ነዋሪዎች የሚያገኟቸው የፋይዳ አገልግሎቶች በአንድ የተጠቃለሉበት ይህ የሞባይል መተግበሪያ በተቁሙ ባለሙያዎች እንዲለማ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በአንድሮይድ እና በኣይኦኤስ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ለሕዝብ ይፋ መደረጉን ተቋሙ አስታውቋል።
መተግበሪያውን ከአፕ ስቶር እንዲሁም ከፕሌይ ስቶር ላይ በማውረድ መጠቀም እንደሚቻልም ተገልጿል።
በዚህም ነዋሪዎች የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም በተለያየ ምክንያት የጠፋባቸውን ወይም ያልደረሳቸውን የፋይዳ ቁጥር ወዲያውኑ መልሰው ማስላክ እንዲሁም፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያቸውን በዲጂታል መልኩ ማግኘት ወይንም አውርዶ መያዝ ይችላሉ ተብሏል።
በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት በባለሙያ ምክንያት የተሳሳተን የሥነ ሕዝብ መረጃ በስልካቸው ማረም፣ የአድራሻ እና የኢሜይል ለውጥ ሲኖር ማደስ እንዲሁም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በካርድ መልክ አሳትሞ ለመያዝና የካርድ ህትመት ማዘዝ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህም ባለፈ ነዋሪዎች የተለያዩ አስተያየት እና ቅሬታቸውን ለመስጠት እንዲሁም የደንበኞች አገልግሎትን ለማግኘት የሚችሉበት፤ ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ የሞባይል መተግበሪያ መሆኑን ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታውቋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን እስካሁን ድረስ 12 ሚሊዮን ዜጎችን ባለቤት በማድረግና ከተቋማት ጋር ሲስተሞችን በማስተሳሰር የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ እና ዘመናዊ መልኩ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የፋይዳ አገልግሎቶችን አጠቃሎ የያዘ የፋይዳ ሞባይል መተግበሪያ ይፋ ተደረገ
