ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አካል ጉዳተኞች በመንግሥትም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ያለው አመለካከት እንደ ተረጂ እንጂ ባለመብት ተደርገው እየታዩ ባለመሆኑ፤ እኩል የሆነ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን መብቶች ኮሚሽነር እርግበ ገብረሃዋሪያ፤ "በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸደቀውን የአካል ጉዳተኞች መብት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም፤ በተሳሳተ አመለካከት ምክንያት እኩል የሆነ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ተፅእኖ አሳድረዋል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

አክለውም "በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንድሁም ማህበራዊ እንቅስቀሴ ላይ እኩል የሆነ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መመሪያ ቢደነገግም ተግባራዊ እየሆነ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተለያዩ ቦታዎች አካል ጉዳተኞች መብታቸው እንዲጠበቅና በሁሉም ዘርፎች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በሚያደርገው ክትትል መሰረት፤ በተሳሳተ አመለካከት ችግር የሚጠይቁት ነገር መብታቸው ሆኖ እያለ እንደ ተረጂ ተደርገው የሚቆጠሩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን እየሰሩ እንደሆነ አንስተው፤ ለማህበረሰቡም የግንዛቤ ትምህርቶችን በሰፊው መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የአመለካከት ችግር በዕለት ተእለት ሥራቸው ላይ ተግዳሮት እንደሆነ ወ/ሮ እርግበ ገብረሐዋርያ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸደቀውን መብት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም በሁሉም የሥራ ዘርፎች ላይ ተጠቃሚ እንድሆኑ ከሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡