ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሦስት ዓመት በፊት በተጠና ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በሚከናወኑ ሕገ-ወጥ እርዶች ምክንያት በዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለአሐዱ ተናግረዋል።
ኃላፊው እንደገለጹት ድርጅቱ በዋናነት ሕገ-ወጥ እርድ ምክንያት በዜጎች ላይ የጤና፣ የኢኮኖሚና መሰል ችግሮችን የሚያስከትል በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም ከነበረው ሕገ-ወጥ የእርድ አገልግሎት አንጻር ለውጦች መኖቸውን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ነገር ግን አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ የእንስሳት እርድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የቆዳ እና ሌጦ ውጦቶችን ጥራት እና ደህንነት ለማስጠበቅ ሕገወጥ የእንስሳት እርድን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለመጪው የገና በዓል 3 ሺሕ የቀንድ ከብት እንዲሁም ከአንድ ሺሕ ፍየልና በግ በላይ ለእርድ ማዘጋጀቱን የገለጹት ኃላፊው፤ ለበዓሉ የሰው ኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ከ1 ሺሕ 100 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች መቀጠራቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለኅብረተሰቡ ንፅህናውን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በፍጥነት እና በቅልጥፍና ለማቅረብ የእርድ መሳሪያዎች እንዲሁም 45 የድርጅቱ የስጋ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የጥራት ጉድለት ክፍተቶችን ለመፍታት ሕገ-ወጥ የእርድ አገልግሎትን ማስወድ እንደሚገባ አንስተዋል።
በበዓሉ ወቅት ሊያጋጥም የሚችል ሕገ-ወጥ የእንስሳት እርድን ለመቆጣጠር ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባስልጣንና፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር ግብርና ኮሚሽን ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሕገ-ወጥ የእንስሳት እርድ ምክንያት በዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚታጣ ተገለጸ
በመጪው የገና በዓል ለሚከናወኑ የእንስሳት እርዶች አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል