ታሕሳስ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዋሽ ባንክ የመጀመሪያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የባንኩ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳበ ህልፈተ ህይወት ምክንያት የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የማኔጅመንት አባላት እና መላዉ ሰራተኞች የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን ገልጿል።
ባንኩ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን ህልፈተ ሕይወት አስመልክቶ ለአሐዱ በላከው የሃዘን መግለጫ፤ "አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በህይወት በነበሩበት ዘመን የትላልቅ ስኬቶች ባለቤት የነበሩና ትልቅ የሀገር ባለ ዉለታ ነበሩ።" ብሏል፡፡
አቶ ቡልቻ "በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው ሰው ነበሩ" ያለው መግለጫው፤ የሀገራችን የፋይናንስ ምክትል ሚንስትር ሆነው ያገለገሉ፤ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሰሩ ትልቅ የሀገር ሃብት እንደነበሩም አስታውሷል፡፡
ባኩ አክሎም፤ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሕልፈተ ህይወት የተሰማንን ሀዘን ገልጾ፤ "ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም ለመላዉ የሀገራችን ህዝቦች መጽናናትን እንመኛለን።" ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳላቸው በበርካቶች የሚነገርላቸው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፤ በዛሬው ዕለት በ94 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡