ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ የሚያስችልና በታክስ ኦዲት የሚወሰኑ ውሳኔዎች በድጋሚ ኦዲት በማድረግ የውሳኔ ጥራት ማረጋገጥ ሥራን የሚሰራ፤ አዲስ የታክስ ኦዲት ጥራት አረጋጋጭ ዘርፍ ማቋቋሙን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት አዲሱ አደረጃጀት አስፈላጊ ዝግጅቶች ተደርገውለት ወደ ተግባር መግባቱን ቢሮው በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

"የኦዲት ጥራት አረጋጋጭ አደረጃጀቱ በዋናነት በባለሙያና በግብር ከፋይ ዘንድ ያለውን ብልሹ አሰራር የሚቀርፍ ነው" ሲሉ የቢሮዉ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም፤ ከዚህ በፊት የኦዲት ጥራት አረጋጋጭ የሥራ ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት የታክስ አሰባሰብ ለብልሹ አሰራርና ሌብነት ተጋላጭ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

አደረጃጀቱ የተቋቋመው በማዕከል መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለቢሮው ኃላፊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት በሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በታክስ ኦዲተሮች የሚወሰኑ የግብር ውሳኔዎች፤ በአዲሱ የሥራ ክፍል ዳግም የሚረጋገጡ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተሰራው ምርመራ በብልሹ አሰራርና ሌብነት የተገኙ ባለሙያዎችና ኃላፊዎችን ጨምሮ በቢሮው እርምጃ የተወሰደባቸው መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፉት 6 ወራት 77 የሚሆኑ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

አክለውም እርምጃ ከተወሰደባቸዉ መካከል 8ቱ የሥራ ኃላፊዎች እንደሆኑና ሌሎች ደግሞ የቢሮው ባለሙያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

"እርምጃውም ከሥራ ማባረርንና በሕግ ተጠያቂ ማድረግን ይጨምራል" ያሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅትም በሕግ እየታዩ ያሉ ጉዳዮች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ