ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የቀድሞው የሰላም ሚንስትር ብናልፍ አንዷለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤና የሥራ መመሪያ ተቀብለዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለአምባሳደር ብናልፍ አንዷለም የሥራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚመጥን ትጋትና ቁርጠኝነት የተላበሰ አመራር መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንቱ "የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ መሾም የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ሃላፊነትና አደራ መጎናጸፍ ነው" ብለዋል።

Post image

ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ዘመን ግንኙነትን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት ሀገር በመሆኗ፤ በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ጠንካራ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

Post image

በመሆኑም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም አሜሪካ ትልቅ እሳቤን የሚጠይቅ ዲፕሎማሲ የሚከናወንባት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ አመራር እንዲሰጡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ወዳጅን ማብዛት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በቀጣናው ሰላምና ትብብርን ለመፍጠር ጠንካራ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

Post image

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ውጤታማነት ከአሜሪካ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በቀጣይ በሰላም፣ በጸጥታና በዳያስፖራ ጉዳዮች ዙሪያ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት አምባሳደር ብናልፍ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ማሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Post image

አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አማካኝነት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ