የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከዓለም አቀፍ የፖሊዮ ማጥፋት ፕሮግራም እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከየካቲ 14 እስከ የካቲት 17 ድረስ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትቫት ዘመቻ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

በኢንስትቲዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ ሚኪያስ አላዩ የክትባት ዘመቻውን ሂደት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ክትባቱን የሚሰጡት ባለ ድርሻ አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን ከ3 ወር በፊት እንደጀመሩና የተሳካ ቅድመ ዝግጅት እንዳካሄዱ ገልጸዋል፡፡

የተቀናጀ የክትባት ዘመቻው በሁለት ዙር የሚሠጥ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር በ10 ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሀረሪ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ 13 ሚልዮን 861 ሺሕ 93 ሕጻናት ይሰጣል ተብሏል።

ፖሊዮ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ክትትል እንደሚያስፈልገው የገለጹት ሚኪያስ አላዩ፤ "በቅርቡም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች እና በአጎራባች ሀገሮች ጭምር የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ እና እየተስፋፋ መምጣቱ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል" ብለዋል።

በመሆኑም ስርጭቱን ለመግታት ብሎም ለማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ የክትባቱን አሰጣጥ ያብራሩ ሲሆን፤ ለዘመቻው መሳካትም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም ይህ ትባት በተሰጠው ጊዜ ገደብ ብቻ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፤ ሌሎች ክትባቶች ደግሞ በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር ሳይወስዱ የቀሩና ጀምረው ላቆረጡ ሕጻናት በጤና ተቋማት እንደሚሰጡ ተመላክቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ