የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የማስተማሪያ ሆስፒታል ለኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት መሻሻል ያበረከቱት አስተዋፅኦ በቀላሉ ተነግሮ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዓታው ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት በተከናወነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተማሪዎች የምርቃት መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

በመልዕክታቸውም የዩንቨርስቲውን አስተዋፅኦ ሲያብራሩ፤ "በርካቶቻችን ከዚህ ዩኒቨርስቲ በወጡ መምህራን ተምረናል፣ በርካቶቻችን በዚሁ ዩንቨርስቲ ተምረናል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ ዩንቨርስቲ ታክመዋል፣ ድነዋል በርካታ ዜጎቻችን ለዚህ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቀስመው ወጥተዋል" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በርካታ ምርምሮች በዩንቨርስቲው መደረጋቸውን በማንሳት፤ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠቃሚ የሆኑ እጅግ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና ዩኒቨርስቲውንና ማኅበረሰቡን ያገናኙ ሰፊ የልማት ሥራዎች በዩንቨርስቲው ስለመሰራታቸው ተናግረዋል፡፡

"ትምህርት ለሁሉም ነገር መሠረት ነው" ያሉት ሚንስትር ዴዔታው፤ ያለ ትምህርት ያደገ የትኛውም አገር የለም፡፡ የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው አገራት የበለፀጉት እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት በትምህርት ላይ በሰሩት ሥራ ባመጡት ለውጥ ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት መንግሥት ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፤ ለበርካታ ዘመን የነበረውን የትምህርት ስብራት በመጠገን በአጠቃላይ ትምህርት እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ላይ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይ የመውጫ ፈተና በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ በመወሰኑ፤ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት የተገኙ መሻሻሎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም "ዘንድሮ በዩንቨርስቲ የመውጫ ፈተና ከፍተኛ ውጤትን በማስመዝገብ፤ የዩኒቨርስቲውን ሥም ያስጠራችሁ ተማሪዎች መምህራንና አጠቃላይ የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ በየመውጫ ፈተና ላይ ከፍተኛ ለውጥ ስላመጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል፡፡

"የሕክምና ደመወዝ የማኅበረሰቡ ከበሽታ መዳን እና ጤናማ መሆን ነው፡፡ የሐኪም ደመወዝ ማኅበረሰቡ የሚያገኘው ደስታ እና እርካታ ነው" ያሉት ዶ/ር ደረጄ፤ "ምንም ያክል ቢከፈል ለሐኪሞቻችንና ለጤና ባለሙያዎቻችን በቂ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ትምህርት አድካሚ የሆነበት ምክንያት በቀጥታ ከሰው ሕይወት ጋር የተገናኘ ከመሆኑም ባሻገር፤ በአጠቃላይ በሀገራችን ለሚፈልገው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑን ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

"ይህ ከመሆኑም የተነሳ ይህንን ከባድ ተልዕኮ በአግባቡ ወስዳችሁ ባለፉት በርካታ ዓመታት ትምህርታቸውን በትጋት የጨረሳችሁ ተመራቂ ተማሪዎች፤ ቀጣዩ የሕይወታቸው ምዕራፍ ቀላል ላይሆን ይችላል" ብለዋል፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ "ተመራቂዎች ከራሳቸው በላይ ለማህበረሰባችሁ፣ ለሕዝባችሁና ለሀገራቸውና የምታስቡበት፤ ኃላፊነትን የበለጠ የምትለማመዱበትና ኃላፊነትን የምትሸከሙበት እንዲሁም ያገኛችሁትን ዕውቀት እና ክህሎት መነሳችሁ ለማህበረሰባቸሁ የምትሰጡበት በመሆኑ ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት "ተመራቂ ተማሪዎች ቀጣይ ሕይወታችሁ የትኛውንም ተግዳሮት ለመጋፈጥና የትኛውንም ውጣ ውረዶችን ለመቀበል መዘጋጀት አስፈላጊ ይሆናል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

"ተመራቂዎች ከሌሎች የጤና ሙያተኞችና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን አካባቢያችሁን እንድትቀይሩ፣ ኃላፊነትን እንድትወስዱና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንድታደጉ አደራ ማለት እፈልጋለሁ" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ