ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ካሉት 41 ባቡሮች እየሠሩ ያሉት 16ቱ ብቻ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሀን አበባው ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ወደ ሥራ ሲገባ 41 ባቡሮች የነበሩት ቢሆንም አሁን አገልግሎት እየተሰጡ ያሉት ባቡሮች ቁጥር 16 ብቻ ነው፡፡

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ባቡሮች አገልግሎት የማይሰጡት በብልሽት ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

ባቡሮቹ ብልሽት በሚያጋጥማቸው ጊዜ የጥገና ዕቃዎች ገበያ ላይ የሉም ያሉት ኃላፊው፤ ችግሩን ለመፍታት ከአንዱ ባቡር እየተነቀለ ወደ ሌላኛው ሲገጠም መቆየቱን ተናግረዋል።

Post image

የባቡሮቹን ሶፍትዌር ለመጠቀም ፍቃድ አለመኖሩም ለባቡሮቹ መቆም ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተበላሽተው የቆሙ ባቡሮችን ወደ ሥራ ለማስገባት፣ የተሻለ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እና ዘርፉ አሁን ካለበት የውጤት መቀዛቀዝ ለማውጣት የሪፎርም ሥራዎች መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የቆሙ ባቡሮችን ወደ ሥራ ማስገባት በሚሰራው ሥራለ፤ እስከ መጪው ሰኔ ድረስ አምስት ባቡሮች ወደሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የሁለት ባቡሮች የጥገና ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ እነኝህ ባቡሮች በቀጣይ ሦስት ቀናት ወደ ሥራ እንደሚገቡ አብራርተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ