ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በተሽከርካሪ አደጋ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አስቸኳይ ሕክምና እንዲሰጥ የሚያዝዘውን መመርያ ተከትሎ፤ ለሚሰጡት አገልግሎት በፍጥነት ክፍያ ስለማይፈጸምላቸው ቅሬታ እያቀረቡ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ተቋማቱ የአገልግሎት ክፍያ እየዘገየብን ነው ሲሉ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ፤ በፌዴራል መንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የድኅረ ትራፊክ አደጋና መድን አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጫላ ፈይሳ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

"በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የሚከፈለውን የአረቦን ተመን የካሳ መጠን ክፍያ ለመወሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ ቁጥር 554/2016 የክፍያ መጠኑን ከፍ ያደረገ ቢሆንም፤ የሕክምና ተቋማት እርዳታ ቢሰጡም ክፍያ እንደሚዘገይባቸው እየገለፁ ነው" ሲሉ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች እና ለተጎጂ ቤተሰቦች ሲሠጥ የቆየው የካሳ መጠን መሻሻሉን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፈ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተሻሻለው ደንብ በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለአስቸኳይ ሕክምና ይከፈል የነበረውን 2 ሺሕ ብር ወደ 15 ሺሕ ብር እንዲሁም፤ ለሞት አደጋ ይከፈል የነበረውን የ40 ሺሕ ብር ካሳ መጠን ወደ 250 ሺሕ ብር ከፍ እንዲደረግ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡