ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከአንድ ዓመት በፊት መካሄድ የጀመረው የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግሥት እድሳት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን ተከትሎ፤ ቅርሱን ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ የሚገቡ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ የቅርስ ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል።

ቅርሱ ከ1980 ጀምሮ ምንም እድሳት እና ጥገና ሳይደረግለት ቆይቶ ባሳለፍነው ዓመት ጥገናው መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ እድሳቱ ሦስት አይነት ሥራዎችን ያካተተ ስለመሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ይህም እድሳት የመጀመሪው ሙሉ ጥገና፣ ሁለተኛው ግቢውን ማስዋብ እና ሦስተኛው የኤሌትሪክ ሀይል የመስመር ዝርጋታን ያካተተ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ፋሲለደስ እንደተቆረቆረች በሚነገርላት ጎንደር ከተማ የሚገኘው እና ከ40 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ‹‹የዓለም ቅርስ›› ተብሎ የተመዘገበው የፋሲል ቤተ-መንግሥት የቅርስ ጥበቃ እና እድሳት ሂደትን በተከተለ መንገድ መታደሱን ለአሐዱ የተናገሩት የጎንደር ከተማ የቅርስ ጥበቃ ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ዓይቼው አዲስ ናቸው።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተካሄደው የቅርሱ እድሳት ተጠናቆ ጎብኚዎችን ማስተናገድ ከጀመረ ወዲህ ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ቁጥር ከሌሎች ጊዜያት አንፃር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

Post image

አክለውም "እድሜ ጠገቡ የፋሲል ቤተ-መንግሥት እድሳት መጠናቀቁ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ከሆኑት እድሜ ጠገብ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ጎንደር ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል" ብለዋል።

"በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እያንሰራራ ይገኛል" ያሉት አቶ ዓይቼው፤ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች ከተማዋን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ፋሲል ግቢ በ1628 ዓ.ም. የተሠራ ሲሆን፤ በውስጡ ቤተ መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ራስ ግምብና ደረስጌ ማርያምን ይዟል፡፡

በዩኔስኮ 1979 ዓ.ም በዓለም ቅርስነው የተመዘገበው የአፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት፤ በውስጡ ያሉት ቤተ መንግሥቶች ከ100 በላይ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን፤ በአጠቃላይ 7 ሄክታር ወይንም 70 ሺሕ ስኩየር ሜትር ይሸፍናሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ