ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ አዛን በማድረግ የመጀመሪያው ነው ተብሎ የሚታሰበውን የቢላል አዛን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የዘይድ ኢብኑ ሳቢት የቁርዓን ማህበር ገልጿል።
ለዚህም በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥናትና የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ኑረዲን ቃሲም ለአሐዱ ተናግረዋል።
"አዛን ሌሎች ሀገራትም 'የእኛ ነው' እያሉ ይገኛሉ" ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሙያዊ ሥራዎችን በጋራ በመስራት በኢትዮጵያ ሥም እንዲመዘገብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በማህበሩ አዘጋጅነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚካሄደው ሁለተኛው የቁርዓንና አዛን ውድድርና የሽልማት መርሐ ግብር በኢትዮጵያ መከናወኑ ደግሞ፤ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ትልቅ ተፅእኖ ይፈጥራል ነው የተባለው።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የቢላል አዛንን ለማስመዝገብ በሚደረገው ሥራ ላይ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ኡስታዝ ኑረዲን ቃሲም ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ